በባሌ ዞን በክረምቱ የተገነቡ 46 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ዝግጁ ሆነዋል

ሮቤ፤ መስከረም11 /2016 (ኢዜአ):- በባሌ ዞን በክረምቱ ወራት የተገነቡ 'ቡኡራ ቦሩ'  የተሰኙ 46 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለዘንድሮ የትምህርት ዘመን ዝግጁ መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በዞኑ ካለፈው በጀት ዓመት መገባደጃ አንስተው በክረምቱ የተከናወኑት የትምህርት ቤቶች ደረጃ የማሻሻል ሥራም የተማሪዎች የቅበላ አቅም ከማሻሻሉም በላይ ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት እንደሚፈጥሩ ተገልጿል። 

የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጸጋ አለማየሁ እንደገለጹት በዞኑ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻል ስራ እና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ጎን ለጎን ሲከናወኑ ቆይተዋል።

በዚህም በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ባለፈው ዓመት ክረምቱን ጨምሮ በህዝብ ተሳትፎና በመንግስት በጀት 46 'ቡኡራ ቦሩ' የተሰኙ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ተከናውኗል ነው ያሉት።

ትምህርት ቤቶቹም በተያዘው የትምህርት ዘመን ህጻናትን ተቀብለው ለማስተማር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በተመሳሳይ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻሉ ተግባር በስፋት መከናወኑን ገልጸው፤ በዚህም 120 አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታና ጥገና እንዲሁም 97 የመምህራን መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል። 

በተጨማሪም 1 ሺህ የሚጠጉ የተማሪዎች መቀመጫ ወንበሮችና 20 ኮምፒዩተሮችን በመጠገን ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ መቻሉን አክለዋል። 

አቶ ጸጋ እንዳሉት፣ የትምህርት ቤቶች ግንባታና ደረጃ ማሻሻል ስራው በአዲሱ የትምህርት ዘመን ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ  50 ሺ ህጻናትን የመቀበል አቅም ፈጥሯል። 

የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻል ስራው ምቹ የመማር ማስተማር ሂደትን ከማሳለጥ በተጓዳኝ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትልቅ እገዛ እንዳለውም አመልክተዋል። 

ለትምህርት ዘመኑ የሚያስፈልጉ የትምህርት ግብዓቶችን ከማሟላት አንጻርም በህብረተሰብ ተሳትፎ በርካታ ስራዎች መከናወኑን ጠቁመዋል። 

በዞኑ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተከናወኑት የትምህርት ቤቶች ማሻሻልና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች 560 ሚሊዮን ብር በሚገመት የህዝብ ተሳትፎና የመንግስት በጀት መከናወናቸውንም ገልጸዋል።  

በዞኑ ጎባ ወረዳ ነዎሪዎች መካከል አቶ ሀሰን አብደላ በሰጡት አስተያየት፣ በአካባቢያቸው የተገነቡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ህጻናት ከአካባቢያቸው ሳይርቁ መሰረታዊ ትምህርት በጊዜ እንዲቀስሙ ዕድል ይፈጥራል። 

የትምህርት ቤት መሰረተ ልማት በህብረተሰብ ተሳትፎ ለማመቻቸት  የተቋቋመው ኮሚቴ አባል ሆነው ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተጎዱ የመማሪያ ክፍሎች መጠገናቸውንም አውስተዋል። 

በባሌ ዞን በ2016 የትምህርት ዘመን እስከ አሁን ከ290 ሺህ 900 የሚበልጡ ተማሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 134 ሺህ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ከዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት የተገኛው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም