የአልጄሪያ አየር መንገድ ከአልጀርስ ወደ አዲስ አበባ የመጀመሪያውን የቀጥታ በረራ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአልጄሪያ አየር መንገድ ከአልጀርስ ወደ አዲስ አበባ የመጀመሪያውን የቀጥታ በረራ አደረገ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2016(ኢዜአ)፦የአልጄሪያ አየር መንገድ ከአልጀርስ ወደ አዲስ አበባ የመጀመሪያውን የቀጥታ በረራ ዛሬ አድርጓል።
በዚሁ በረራ በአልጄሪያ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዮሴፍ ቻሮፍ የተመራ የአልጄሪያ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገብቷል::
የልዑካን ቡድኑ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፣ በኢትዮጵያ የአልጄሪያ አምባሳደር ሞሃመድ ላምኔ ላባስን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል::
ኢትዮጵያና አልጄሪያ እ.አ.አ በ1985 የአየር በረራ አገልግሎት ስምምነት የተፈራረሙ ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል።
በዚሁ መሰረት በሁለቱ ሀገራት መካከል የቀጥታ በረራ እንዲኖር ለማስቻል ከዚህ ቀደም የተፈረመው ስምምነት አሁናዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ ታድሶ ወደ ስራ እንዲገባ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
በኢትዮጵያና አልጄሪያ መካከል የትራንስፖርትና አቪዬሽን ዘርፉን ትስስር ለማጠናከር በቅርቡ በሁለቱ ሀገራት መካከል መግባባት ላይ መደረሱ ይታወሳል፡፡
ዛሬ የተጀመረው በረራ ስምምነቱን ወደ ተግባር ለመቀየሩ አንዱ ማሳያ መሆኑም ተመላክቷል::
የኢትዮጵያና የአልጄሪያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የተመሠረተው እ.አ.አ በ1960 ዎቹ ሲሆን አልጄሪያ ኤምባሲዋን እ.አ.አ በ1976 በአዲስ አበባ ከፍታለች ::