በአማራ ክልል በቢራ ገብስ ከለማው መሬት ከ282ሺህ 400 ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል

ባህር ዳር፤ መስከረም 11 ቀን  2016(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በመኸሩ ወቅት በቢራ ገብስ ከለማው መሬት ከ282 ሺህ 400 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። 

የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ አግደው ሞላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመኽር ወቅቱ  በክልሉ እየለማ ካለው የሰብል ዓይነት ውስጥ የቢራ ገብስ አንዱ ነው።

በወቅቱ በ12 ሺህ 270 ሄክታር መሬት ላይ የቢራ ገብስ  መልማቱን አመልክተው ከዚህም የሚጠበቀው ምርት  ከ282 ሺህ 400 ኩንታል  በላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

ክልሉ በቢራ ገብስ የመልማት ሰፊ አቅም እንዳለው ጠቅሰው፤ የአርሶ አደሩ በቢራ ገብስ የማልማት ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

ልማቱን ውጤታማ ለማድረግም  የግብርና ባለሙያዎች  ለአርሶ አደሩ ክትትልና ድጋፍ እየተደረጉ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ ሳርና ቀበሌ አርሶ አደር የማታ ቢሰጥ በሰጡት አስተያየት፤ በመኸሩ ወቅት   ሩብ ሄክታር መሬት ላይ ቢራ ገብስ አልምተው እየተንከባከቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

አንድ ኩንታል ቢራ ገብስ በ6 ሺህ 500 ብር ለማስረከብ ደብረታቦር ከተማ ከሚገኘው መገናኛ ዩኒየን ጋር የውል ስምምነት ይዘው እየሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።


 

በዘር ከሸፈኑት መሬት እስከ አስር ኩንታል ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን ጠቅሰው፤  አሁን ላይ ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ግማሽ ሄክታር መሬት በቢራ ገብስ እያለሙ መሆናቸውን የተናገሩት  ደግሞ በዚሁ ወረዳ የማይናት ቀበሌ አርሶ አደር ያለለት ሞላ ናቸው።

 አሁን ላይ ሰብሉን ከአረምና ፀረ ሰብል ተባይ እየጠበቁ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

የመገናኛ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋየ አየነው በበኩላቸው፤ ዩኒየኑ በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣና ጉና ወረዳዎች ቢራ ገብስ የሚያለሙ አርሶ አደሮች ጋር ቀድሞ ውል በመያዝ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

አንድ ኩንታል የቢራ ገብስ በ6 ሺህ 500 ብር ለመረከብ ውል መያዛቸውንና አርሶ አደሮች የምርታቸውን ጥራት ጠብቀው ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት ከለማው መሬት 303 ሺህ ኩንታል የቢራ ገብስ በማምረት ለጎንደር ብቅል ፋብሪካ ማቅረብ እንደተቻለ ተመላክቷል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም