አውደ-ርዕዩ በዘርፉ ያካበተ ልምድ ካላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት እድል ፈጥሯል -  የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 11/2016 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ለአንድ ወር የተካሄደው የውኃና ኢነርጂ አውደ-ርዕይ በዘርፉ ያካበተ ልምድ ካላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት እድል መፍጠሩን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ። 

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር "የውኃ ኃብታችን ለብልጽግናችን" በሚል መሪ ኃሳብ በሳይንስ ሙዚየም ለአንድ ወር ያካሄደው አውደ ርዕይ ትላንት ተጠናቋል።

አውደ ርዕዩ ምን አስገኘ? የሚለውን ለማወቅ ኢዜአ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በአውደ-ርዕዩ አገልግሎታቸውን ያቀረቡ ተቋማትን አነጋግሯል።   

በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ጌትነት ጌጡ፤ በአውደ-ርዕዩ ዘርፉን ለማዘመን በትግበራ ላይ ያሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለዕይታ ቀርበዋል ብለዋል።   

ለአብነትም ኢትዮጵያ የውኃ መጠኗን በዲጂታል መተግበሪያ በመታገዝ እንዴት እንደምትከታተልና እንደምትቆጣጠር ማሳየት መቻሏን ጠቁመዋል።   

አውደ-ርዕዩን የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጨምሮ የዘርፉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም አምባሳደሮች መጎብኘታቸውን ነው ያረጋገጡት።   

በመሆኑም አውደ-ርዕዩ አገሪቱ በዘርፉ የምታከናውነውን ሥራ ለማስገንዘብ እድል ሰጥቷል ነው ያሉት።

ከዚህ በተጠማሪም  አውደ-ርዕዩ በዘርፉ ከተለያዩ ተቋማት ጋር አዳዲስ አጋርነትና ትብብር ለመመሥረት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ገልጸዋል። 

በመድረኩ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ያቀረቡ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በበኩላቸው አውደ-ርዕዩ የውኃና ኢነርጂ ዘርፍን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሠሯቸውን ሥራዎች ለሕዝብ ለማቅረብ እድል ሰጥቶናል ብለዋል። 

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በመረጃና ክላይማቶሎጂ ክፍል ተመራማሪ የሆኑት ለታ በቀለ ተቋማቸው በአውደ-ርዕዩ በአገሪቱ ያለውን የአየር ፀባይ ሁኔታ ጥናት ለማካሄድ የሚጠቀምባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አውደ-ርዕዩን መጎብኘታቸው ገልጸው ይህም በቀጣይ በሚቲዎሮሎጂ ዘርፍ አብረው መሥራት የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ለመለየት ዕድል መፍጠሩን ነው የገለጹት። 

የአነጋ ኢነርጃይዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የሽያጭ ባለሙያ እየሩሳሌም ደጀኔ በበኩሏ በአውደ-ርዕዩ ኅብረተሰቡ የሚጠቀምባቸውን ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎች ማቅረባቸውን ተናግራለች።

በዝግጅቱ ላይ መሳተፋቸው ኃይል ቆጣቢ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በቀላሉ ለማስተዋወቅ እንደረዳቸው በመግለፅ እንደ አገር መሰል አውደ-ርዕዮች በተለያዩ አካባቢዎች ሊስፋፉ እንደሚገባ ተናግራለች።

በሐፍ አስመጪና አቅራቢ ድርጅት የኦፕሬሽን ማናጀር ሃበን ገብሩ በአውደ-ርዕዩ ምንም አይነት ኤሌክትሪክ ኃይልና የውኃ ማጣሪያ ኬሚካል ሳይጠቀም ውኃን ማጣራት የሚችል ቴክኖሎጂ ለኅብረተሰቡ በስፋት አሳይተናል ብለዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም