የቱሪዝም ሚኒስቴር በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አምስት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን እንደሚያስገነባ አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2016(ኢዜአ)፦የቱሪዝም ሚኒስቴር በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አምስት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን እንደሚያስገነባ አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግኑኙነት ዳይሬክተር ዶክተር ዓለማየሁ ጌታቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም አቅም በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ ማዋል ሳትችል ቆይታለች፡፡

በመሆኑም አሁን ላይ መንግስት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን በማስተዋወቅ ከዘርፋ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት። 

በዚህም የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ጎብኝዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን  ተናግረዋል። 

የቱሪዝም ፍሰቱን ይብልጥ ለማሻሻልም የነባር የቱሪዝም ስፍራዎችን ማደስና አዳዲስ የማልማቱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት፡፡

ከዚህ አኳያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ህዝብን በማስተባበርና የፋይናንስ ምንጮችን በማፈላለግ አምስት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማት ስራ እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡  

የሚለሙት የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች በቀጣይ ይፋ እንደሚደረጉም ነው የተናገሩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ "በገበታ ለሀገር" እና "በገበታ ለትውልድ" አማካኝነት እያከናወኗቸው ያሉ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማት ስራ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ በእጅጉ እንደሚያሻሻልም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም