ቢሮው ከበጎ ፈቃደኞች ያሰባሰበውን የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ ልጆች እያከፋፈለ መሆኑን ገለጸ

157

አዳማ፤ኢዜአ መስከረም 11/2016፡- የኦሮሚያ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ከበጎ ፈቃደኞች ያሰባሰበውን የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ ልጆች እያከፋፈለ መሆኑን ገለጸ።

የኦሮሚያ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ሰሚራ ፋሪስ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትና በትምህርት ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዳይሆኑ ሲሰራ ቆይቷል።

''አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ'' በሚል መሪ ቃል በክረምቱ ከክልሉ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጀምሮ እስከ ወረዳ፣ ከተሞችና ዞኖች ድረስ የዘላቂ ንቅናቄ በማካሄድ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

የክልሉ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀት፣ ባለሃብቶችና የክልሉን ነዋሪ በማስተባበር ደብተር፣ እስክሪፕቶ እና ቦርሳዎች፣ አልባሳትና ጫማዎች መሰብሰብ መቻሉን አንስተዋል።


 

ከተለያዩ አካላት ተሰባስቦ እየተከፋፈለ ያለው የትምህርት ቁሳቁስ ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያለው ነው ብለዋል።

የተሰበሰበው የትምህርት ቁሳቁስም ከ2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የአቅመ ደካማ ወላጆች ተማሪዎች እየተከፋፈለ መሆኑን አብራተዋል።

በተጨማሪም ህፃናት በምግብ ችግር ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ የዘንድሮውን የተማሪዎች ምገባ ለማሳካት ቢሮው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የማስተባበር ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአዳማ ከተማ የገዳ ሮበሌ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ምንዳ ረገሳ በበኩላቸው በትምህርት ቤቱ ለሚማሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰብ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

በተለይ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትና በመማር ላይ የሚገኙ ልጆች ደብተር፣ ቦርሳና እስክሪፕቶን ጨምሮ የተለያዩ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ከትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎችና ከበጎ አድራጊ ወጣቶች ጭምር በርካታ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም