በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ኮሌጆች ከረዥም ጊዜ ስልጠና ይልቅ አጫጭር የሙያና የንግድ ሐሳብ ስልጠና ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑ ተገለጸ

አዳማ ፤(ኢዜአ) መስከረም 11/2016:-በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ኮሌጆች  ከረዥም ጊዜ ስልጠና ይልቅ አጫጭር የሙያና የንግድ ሐሳብ ስልጠና ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የክልሉ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ገለፀ ።

ቢሮው በየኮሌጆች እየተከናወኑ ያሉ የፈጠራና የክህሎት ስራዎችን መሰረት ያደረገ ከ6ሺህ 800 በላይ የኢንተርፕረነርሺፕ አሰልጣኞችን ማብቃቱን ገልጿል።

የቢሮው አመራሮች ከኢንተርፕረነርሺፕ አሰልጣኞችና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በመሆን በቢሾፍቱ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተመረቱ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች እንዲሁም ጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን ጎብኝተዋል።

የኦሮሚያ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሀብታሙ ካሣ እንደገለፁት በዘንድሮው ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶችና ሴቶች የሙያና ኢንተርፕረነርሺፕ ስልጠናና ክህሎት ለመስጠት ወደ ተግባር ተገብቷል።

ቢሮው ከግብርና፣ ንግድና ገበያ ልማት፣ ከኮሌጆችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በክልሉ ያሉ የስራ አማራጮችና አቅሞች ላይ ጥናት ማድረጉንም ገልጿል።

በዚህም ሰፊ የስራ ዕድሎችና አማራጮች ቢኖሩም ከጠባቂነት አስተሳሰብ ጀምሮ ማነቆ ሆኖ የቆየውን የወጣቶችም ሆነ የህብረተሰቡ የስራ ባህል መለወጥ እንደሚገባ ጥናቱ ማመላከቱን ተናግረዋል።

ችግሮቹን  ለመቅረፍ ኮሌጆች ከረዥም ስልጠና ይልቅ አጫጭር የሙያና የንግድ ሐሳብ ስልጠና ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚረዱ የስልጠና ስልቶችን ማዘጋጀቱን ነው የገለጹት።


 

ስራ አመራር፣ አማራጭ የገቢ ምንጭ፣ ማህበራዊ ኢንተርፕረነርሺፕና የተቀናጀ የኮሌጆች ኢንተርፕረነርሺፕ ደግሞ የስልጠና ስልቶቹ የተዘጋጁባቸው ዘርፎች መሆናቸውን ምክትል ሃላፊው ገልጸዋል።

በዚህም ወጣቶች፣ ሴቶችና አርሶ አደሮችን ጨምሮ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች በዚህ ዓመት የኢንተርፕረነርሺፕ ክህሎትና የሙያ ስልጠና የሚያገኙ ይሆናል ብለዋል።

አክለውም በዘንድሮው ዓመት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በሙያና ንግድ ልማት የተደገፈ የስራ ዕድል ይፈጠራል ብለዋል።

ለእነዚህ የስራ እድሉ ተጠቃሚዎች ደግሞ የብድር፣ የመስሪያና መሸጫ ማዕከላት፣ የእርሻ መሬቶች፣ ግንባታና ማዕድን ልማት እንዲሁም የማሽን ሊዝ ጭምር ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የቢሾፍቱ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ደበላ ተስፋ እንደገለፁት ኮሌጁ የሙያና የክህሎት ስልጠና ለመስጠት 16 የሙያ አይነቶችን ለይተን ወደ ተግባር ገብተናል ብለዋል።

በተለይም ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ማኑፋክቸሪንግ ወዘተ ዘርፎች ላይ አጭርና ረዥም ስልጠና በመስጠት ኮሌጁ የስራ ዕድል ፈጠራ አማራጮች ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም መስከረም 26 እና 27 ቀን 2016 ዓ.ም በሚከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ከ1ሺህ በላይ በኮሌጁ የተመረቱ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች እንዲሁም ጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት አጠናቀናል ነው ያሉት።

በዚህም በክህሎትና ሙያ የዳበረና ገበያ መር ሰራተኛ ዜጎችን ከመፍጠር ባለፈ ኮሌጁ 28 ሚሊዮን ብር የውስጥ ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
 

በክልሉ የሚገኙ ከ200 በላይ ኮሌጆችን በ22 ክላስተር በማደራጀት ተቋማቱ የገንዘብና የሙያ ምንጭ እንዲሆኑ የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንሼቲቭ ተቀርጾ ወደ ተግባር መገባቱንም የቢሮው መረጃ ያስረዳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም