ያሆዴ- የአዲስ ተስፋና ልምላሜ ምልክት

(በማሙሽ ጋረደው ከሆሳዕና)

ያሆዴ የሃድያ ብሔር የአዲስ ዘመን መሸጋገሪያ በዓል ነው። በዓሉ ሲከበር ቂምና ቁርሾ ተወግዶ ያለፈው ዓመት መልካምና በጎ ያልሆነ ሁኔታ ታይቶ ለቀጣይ ስኬት አዲስ ተስፋና ልምላሜ ሰንቆ የሚሻገሩበት በዓልም እንደሆነ ይነገራል። 

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሃድያ ዞን አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ታምሬ ኤርሚያስ እንዳሉት ሃድያ የራሱ የሆነ የጊዜ አቆጣጠር ባህል፤ ልማድ፤ ወግና ስርዓት አለው። ለዚህም እንደ ማሳያ በብሔሩ ዘንድ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበረውን የያሆዴ ክብረ በዓል ለአብነት ጠቅሰዋል። በዓሉ የአዲስ ተስፋና ልምላሜ ምልክት ተደርጎ እንደሚወሰድ የተገለጸ ሲሆን በተለይም የሚመጣው ዘመን የስኬት እንዲሆን እያንዳንዱ ካለፈው ዓመት ስኬትና ውድቀት ልምድ እየቀመረ ሃገር ሰላም እንዲሆን ተመራርቀው በደስታ እየተበላ፤ እየተጠጣ የሚከበር በዓል መሆኑንም ተናግረዋል።

በብሔሩ ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው የያሆዴ ክብረ በዓል አሮጌውን ዓመት ሸኝተው አዲሱን ዓመት የሚጀምሩበትም ነው። በዓሉ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ ክዋኔዎች የሚከበር ሲሆን በዓሉ መቅረቡን ታዳጊ ልጆች በተለያዩ ገላጭ በሆኑ ድርጊቶች እንደሚያበስሩ አቶ ታምሬ ተናግረዋል። በተለይም ታዳጊዎቹ ያሆዴ  መድረሱን ለማብሰር ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ጳጉሜ መጨረሻ ድረስ በብሔሩ አጠራር ገምባቡያ ወይም (ዋሽንት) በመጠቀም የተለያዩ ጥዑመ ዜማዎችን በማሰማት በዓሉ መቅረቡን ያበስራሉ። 

በሃድያ ብሔር ዘንድ የአዲስ ዘመን ብስራት “ያሆዴ" የብሩህ ተስፋ፣ የሠላም፣ የፍቅር፣ የረድኤት፣ የበረከት ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰድ በዓል መሆኑንም አመልክተዋል።  ይህም የሆነበት ምክንያት በመስከረም ሰውና እንስሳ ከዶፍ ዝናብ፣ ከውርጭ፣ ከጤዛና ከጭቃ፣ ከጉም፤ ከጭጋግና ጽልመት ነጻ ይሆናሉ።  ምድሩ በሃምራዊ ቀለም ደምቆ ያሸበርቃል።  ፀሐይ ሙሉ ገላዋን ገልጣ ጸዳሏን ትሰጣለች።  በመሆኑም በስራ የደከመ ሰውነት ዘና፣ የታመመ ቀና ይልበታል፣ ልጅ አዋቂ የደስታ ነጋሪቱን ይጎስማል፣ የፍቅር ጽዋ ይጠጣል፣ የአእምሮ እርካታ ይነግሳል፣ በሁሉም ነገር ደስታ ይሰፍናል ወርሃ መስከረም በጥጋብና ደስታ ይጀመራል ።


 

በዓሉ ከመግባቱ በፊት የራሱ የሆነ የሥራ ክፍፍል ኖሮት ቅድመ ዝግጅት የሚደረግበት መሆኑን ያነሱት ሃላፊው የቤተሰብ አባላት ሁሉም በየድርሻቸው ሃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሚጠብቁት ተናግረዋል። ለአብነትም ለበዓሉ መድመቅ በዓሉ ከመድረሱ ሦስትና አራት ወራት በፊት በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ የቤተሰብ አባላት የሚወጡት ድርሻ አላቸው። የሃድያ አባቶች የያሆዴን የዘመን መለወጫ በዓል የሚያከብሩት በቅንጅት አማካኝነት ከአራት እስከ ስድስት ሰው በመሆን ተቀናጅተው ሰንጋ በመግዛት ነው። ለበዓሉ ሰንጋ መግዣ የሚሆን ገንዘብ ማስቀመጥ የሚጀምሩትም ቀደም ብለው ነው ።

እናቶች በዓሉ ከመቃረቡ ከሦስትና እና አራት ወራት በፊት ለበዓሉ የሚሆን ቅቤ ለማጠራቀም በሚገቡት (ዊጆ) በተሰኘ ዕቁብ ቅቤ ማከማቸት ይጀምራሉ። በተጨማሪም ለስጋ መብያና ለአተካና መስሪያ የሚሆን እንሰት በመለየትና በመፋቅ፣ ቆጮ፣ ሜሬሮና፣ ቡላን ጨምሮ የሚጠጣ  ቦርዴ፣ ቃሪቦ፣ ጠጅ፣ ብርዝ የማዘጋጀት የድርሻቸውን ይወጣሉ። የደረሱ ልጃገረዶች የቤቱን ወለል ቆፍረው ይደለድላሉ፣ የተለያዩ ውበት የሚሠጡ ቀለማትንና የተለያዩ ኖራዎችን በመጠቀም የቤቱን የውስጥና የውጭ ግርግዳን በመቀባት ያስውባሉ። ወጣቶች ከነሐሴ መግቢያ ጀምሮ አባቶቻቸው የሚመርጡላቸውን ዛፍ፣ ግንድ ቆርጠው  ለምግብ ማብሰያና ለደመራ የሚሆን ችቦ የማዘጋጀት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይቆያሉ።

ከመስከረም መግቢያ ጀምሮ ያሉ የቅዳሜ ገበያዎች ስያሜ (መቻል ሜራ ) የእብድ ገበያ በመባል ይጠራሉ።እነዚህ የግብይት ቀናት ከዚህ ቀደም እንደነበሩ የግብይት ቀናት በተረጋጋ መንገድ የሚተገበሩ ባለመሆኑና በጠዋት ቆሞ በጊዜ የሚበተን ገበያ በመሆኑ (መቻል ሜራ) የእብድ ገቢያ የሚል ስያሜ አሰጥቶታል ነው ያሉት አባቶች  ሰንጋ ገዝተው ለመብላት ባደራጁት (ቱታ) ቅንጃ አማካኝነት ያጠራቀሙትን ገንዘብ በመያዝ ወደ መቻል ሜራ (እብድ ገበያ) በመሔድ የሚፈልጉትን ሰንጋ ገዝተው ይመለሳሉ። ገንዘብ ያላስቀመጡና በወቅቱ ማግኘት የማይችሉ አባወራዎች በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተደስተው እንዲያሳልፉ ሌላኛው አማራጭ (ሃባ) በመባል የሚታወቅና ምንም ገንዘብ የሌላቸው ሰዎች ለበዓሉ የሚሆን ሰንጋ በብድር የሚወስዱበት በብሔሩ ተወላጆች ዘንድ የኖረ የመተጋገዝና የመተሳሰብ እሴት አንዱ ነው።

የሚፈልጉትን ሰንጋ ከመረጡ በኋላ እህል በሚደርስበት በታህሳስና በጥር ለመክፈል በዱቤ ይወስዳሉ። የበሬ ነጋዴውም ያለ ማንገራገር ሰንጋውን በመስጠት ወቅቱ ሲደርስ ገንዘቡን ለመውሰድ ተስማምቶ ይሰጥና ወቅቱን ጠብቆ ገንዘቡን ይወስዳል። በትውስት ተወስዶ ገንዘብ ያልከፈለ አባወራ ለቀጣይ የዘመን መለወጫ አይደርስም ተብሎ በብሔሩ ዘንድ ስለሚታመን በተስማሙበት ወቅት ገንዘቡን የመስጠት ግዴታቸው የተጠበቀ ነው።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የመምሪያው ባለሙያ አቶ ይዲድያ ተስፋሁን እንዳሉት በዓሉ ያለው ለሌለው አካፍሎ በጋራ የሚበላበትና ወደ አዲስ ዘመን በጠንካራ አብሮነት የሚሻገሩበት ነው። በመሆኑም የያሆዴ በዓል በዜጎች መካከል ጠንካራ አንድነትና አብሮነትን መሰረት ያደረጉ ዕሴቶች ያሉበት መሆኑን አንስተው ለትውልድ ግንባታ የሚሆኑ ዕሴቶችን አጎልብቶ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል ። ለበዓሉ ዋዜማ ከሚዘጋጁ ሁነቶች መካከል አተካና ልዩ ቦታ የሚሰጠው ነው። አተካና በተለይም ለዚህ በዓል ከዚህ ባሻገር ለትልልቅ እንግዶች ከሚዘጋጁ  ምግቦች መካከል  አንዱ ነው። አተካና  ከወተት፣ ከቅቤ፣ አይብና ቡላ የሚዘጋጅና በበዓሉ የምግብ ፍላጎትን የሚከፍት ተበልቶ የማይጠገብ በእናቶች የሚዘጋጅ ጣፋጭ ምግብ ነው። የበዓሉ ዋዜማ አተካን ሂሞ (የአተካና ምሽት) የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን በዓሉን ለማክበር ከሩቅም ከቅርብም የተሰበሰበ ቤተሰብና እንግዶች በናፍቆት የሚመገቡት ምግብ ነው።

በዚሁ ዕለት በአካባቢው ትልቅ የሚባል አባወራ (አዛውንት) ቤት ችቦ (ሳቴ )  ተዘጋጅቶ ማምሻውን አባቶች ወይም የሃገር ሽማግሌዎች የማቀጣጠያ (ጦምቦራ) ደመራ ማቀጣጠያ ይዘው ይወጣሉ። ከዚያም የአካባቢው ማህበረሰብም የሃገር ባህል ልብስ ለብሰው እንዲሁም ወጣቶች  ተሰብስበው ያሆዴ ይጨፍራሉ።  የሃገር ሽማግሌዎች ይመርቃሉ፤ ከዚያም የተዘጋጀውን ችቦ በእሳት ለኩሰው ያበራሉ። ይህም አዲስ ዘመን መግባቱን ማብሰርና ዓመቱ  የብርሃን ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞት የሚገለፅበት ነው። ደመራው ከተቀጣጠለ በኃላ ወጣቶች  ያሆዴ (ኦሌ) ጭፈራ ሲጫወቱ ያነጋሉ። ይህ ጭፈራ ከያሆዴ በዓል ውጭ አይጨፈርም። 

ወጣት ደመቀ አባቴ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ ሲሆን ስለ በዓሉ አስተያየቱን ሲሰጥ ''በአባቶች ደመራው ከተቀጣጠለ በኃላ እኛ ወጣቶች  ያሆዴ ....ያህዴ....ሆያ ሆ... /ኦሌ/ ጭፈራ እየተጫወትን እናነጋለን፤'' ይህ ጭፈራ ከያሆዴ በዓል ውጭ ስለማይጨፈር በዓሉን ቀን በጉጉት እንደሚጠብቁት ተናግሯል። ተራርቀው የቆየ ወዳጅ ዘመድ ተሰብስቦ ያለምንም ልዩነት ችግርም ካለ በዕርቅና ሰላምን በማውረድ የሚመጣው ዘመን የልምላሜና የስኬት እንዲሆን ተመራርቀው የሚለያዩበት በዓል በመሆኑ በተስፋ የሚጠብቁት እንደሆነ ነው ወጣቱ የሚናገረው።

የበዓሉ እለት ለዕርድ የተዘጋጀው ሠንጋ ከቀረበ በኃላ የባህል ሽማግሌዎች (ጋቢማ ) ሥርዓት ያከናውናሉ። ክዋኔውም የበሬውን ሻኛ በለጋ ቅቤና በሠርዶ ሳር በመቀባትና ወተት በማፍሰስ ይከናወናል። ይህም በሚከናወንበት ወቅትም  ክፉ ቀን አይምጣ፣ ርሃብ ሰቀቀን ይጥፋ፣ ጥጋብ ይስፈን፣ በአካባቢው በሃገሩ ጥጃ ይቦርቅ፣ ልጅ ይፈንጭበት፣ አገር ሰላም፣ ገበያ ጥጋብ ይሁን፣ ሰማይና ምድሩ ይታረቁን በማለት (ፋቴ)  ዳግም ምርቃት ፈጽመው በሬው ይጣልና የዕርድ ሥርዓት ይካሔዳል። በዕለቱም ከታረደው ሥጋ ቅምሻ በጋራ ይበሉና ቀሪውን ለማህበሩ (ለቱታ) አባላት ክፍፍል ይፈፀማል።

ከእርድ ሥርዓቱ  በኃላ በማግስቱ  ልጆች ወደ ወላጆቻቸው ዘራሮ የሚባል አበባ  ይዘው እየጨፈሩ ያስማሉ -ይመረቃሉ የመስቀል አበባ እንደሚኖር ኑሩ ይባባላሉ፤ ከስጋውም ፣ከቦርዴውም ፣ ከአተካናውም የሚመገቡበት ክዋኔ (ሚክራ) በመባል ይታወቃል። ትዳር የያዙ ሴት ልጆችም ከባሎቻቸው ጋር ሆነው ወደ ወላጆቻቸው ምግብ ሰርተው፣ የሹልዳ ስጋና (ዘራሮ) አደይ አበባ ጭምር ይዘው የሚሔዱበት እንዲሁም ያላገቡ ወጣቶች ለትዳር የሚሆናቸውን አጋር የሚፈልጉበትና የሚያጩበት ባህልም ያለው ነው ያሆዴ ክብረ በዓል። ከእርድ ስነ ስርዓቱ በኋላ ከሶስት ሳምንታት እስከ ወር ለሚሆን ጊዜ  የመጠያየቂያና የመረዳጃ ወቅት ይሆናል።

የያሆዴ በዓል ያሉ ዕሴቶች ለህዝብ ትስስር፣ ጠንካራ የስራ ባህልና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና ለማላቅ በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደምገባ የሚያነሱት በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የህዝብ ግንኙነትና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የአቶ ዳንኤል ገዴ በዚህ ላይ በአከባቢው ያሉ የማህበረሰብ ልምዶችና ወጎች ለትውልድ እንዲሸጋገሩ መስራትና የሃገር በቀል ዕውቀትን ማጠናከር እንደምገበባ ተናግረዋል። በዚህ ረገድ የዋቸሞ ዩኒቨረሲቲ የሃድያን ብሔር የዘመን አቆጣጠር ታሪክ : ባህልና ቋንቋ እንዲሁም ሌሎች ዕሴቶች ተሰንደው እንዲቀመጡና ለማስተማሪያነት እንዲውሉ ለማስቻል  በጥናትና ምርምርና የተደገፈ ስራ በመስራት ላይ መሆኑን አመላክተዋል። በተጨማሪም ባህሉ ይበልጥ እንዲታወቅና በዩኔስኮ ተመዝግቦ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚገባውን ጥቅም እንዲያመጣና ከቱሪዝም አንጻር ሚናውን እንዲጫወት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም