ሉሲዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ሉሲዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከብሩንዲ አቻው ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያካሂዳል ።
እ.አ.አ 2024 በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 15ኛው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት ያካሂዳል።
በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ፤ 26 ተጨዋቾችን በመያዝ ዝግጅቱን ከጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም. አንስቶ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲያደርግ ቆይቷል።
ከአገር ውስጥ ቡድኖች ጋርም የተለያዩ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አድርጓል።
ለዛሬው ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አከናውኗል።
በ38 ዓመቱ ብሩንዲያዊ ጉስታቭ ኒዮንኩሩ የሚሰለጥነው የብሩንዲ ብሔራዊ ቡድን ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር(ፊፋ) ወርሃዊ በሴቶች የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ 124ኛ እንዲሁም ብሩንዲ 175ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ሴንያሴንግ ሴፌ ከቦትስዋና የሁለቱን ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራሉ።
በሁለቱ አገራት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ስምምነት የቡድኖቹ የመልስ ጨዋታ መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚከናወን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የመልሱ ጨዋታ በአዲስ አበባ የሚከናወነው ብሩንዲ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መስፈርቶች የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ማስተናገድ የሚችል ስታዲየም የሌለው እንደሆነ ገልጿል።
በአንጻሩ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም የካፍን መስፈርቶች ያሟላ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።
ሉሲዎቹ በደርሶ መልስ ጨዋታ ካሸነፉ በቀጣዩ ዙር ከዩጋንዳና አልጄሪያ አሸናፊ ጋር ይጫወታሉ።
ሞሮኮ እ.አ.አ በ2024 በምታስተናግደው 15ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ 40 አገራት የማጣሪያ ጨዋታቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የማጣሪያ ጨዋታዎቹ በሁለት ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታዎች የሚከናወን ሲሆን ከአስተናጋጇ አገር ሞሮኮ ውጭ 11 አገራት የተሳትፎ ቦታውን ለማግኘት ይፋለማሉ።
በአፍሪካ ዋንጫ ውድድሩ ላይ 12 አገራት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) አስታውቋል።