በተያዘው ዓመት በክልሉ በ30ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሻይ ቅጠል ችግኝ ይተከላል- ቢሮው

መቱ መስከረም 11/2016 (ኢዜአ):-በተያዘው ዓመት በክልሉ በ30ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ወደ 400 ሚሊዮን የሚጠጋ የሻይ ቅጠል ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በምዕራቡ የክልሉ አካባቢ ከሚገኙ ስድስት ዞኖች ለተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች በሻይ ልማት ዙሪያ በተግባር የተደገፈ ስልጠና ሰጥቷል።

በሻይ ተክል አዘገጃጀት ላይ ያተኮረ በተግባር የተደገፈ ስልጠና የተሰጠውም ከኢሉ ባቦር፣ ቡኖ በደሌ፣ ጂማ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋና ምስራቅ ወለጋ ለተውጣጡ ባለሙያዎች  መሆኑን በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የቡናና ሻይ ልማት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አቦሴ ተናግረዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክልሉ መንግስት ለመስኩ እየተሰጠ ባለው ትኩረት የሻይ ተክል ልማትን በእነዚሁ ዞኖች በማላመድ ረገድ መልካም ጅማሮዎች እየተመዘገቡ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በ2016 በጀት ዓመትም በክልሉ በ30 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ወደ 400 ሚሊዮን የሚደርስ ችግኝ እንደሚተከል ነው ያነሱት።

ዕቅዱን ለማሳካትም ቀድመው  መከናወን ከሚገባቸው ስራዎች አካል የሆነው የባለሙያዎችን ብቃትና ግንዛቤ የማሳደግ ተግባር ተኮር ስልጠና ስራው በስፋት እየተከናወነበት መሆኑን ገልጸዋል።

ተግባር ተኮር ስልጠናውም በኢሉባቦር ዞን በተዘጋጁ የሻይ ችግኝ ጣቢያዎች ላይ መሆኑንም ገልፀዋል።  

የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስጨናቂ አድማሱ ዞኑ በሻይ ልማትና በችግኝ አዘገጃጀት ላይ ያለውን ልምድና ተሞክሮ ለሌሎች አጎራባች ዞኖች በማጋራት ለመስኩ ስኬታማነት የድርሻውን እንደሚወጣ አንስተዋል።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት በሻይ ልማት ዙሪያ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንና በተያዘው ዓመትም ወደ 200 ሚሊዮን የሚጠጉ የሻይ ተክል ችግኝ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

ከተለያዩ ዞኖች መጥተው በስልጠናው ላይ የተካፈሉት ባለሙያዎችም ስልጠናው በሻይ ልማት ዙሪያ የነበራቸውን ክህሎት የሚያሳድግና ክፍተቶቻቸውን የሚሞላ መሆኑን አንስተዋል።

ከጅማ ዞን የመጡት አቶ መሐመድፋቱ አባጎጃም ስልጠናው በዞናቸው የተያዘውን የሻይ ቅጠል ልማት ዕቅድ በስኬት እንዲያከናውኑ የሚረዳቸውን ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን ገልፀዋል።

የችግኝ አዘገጃጀት፣ አተካከልና የእንክብካቤ ተግባሩ ውጤታማ በሆነ መልኩ የሚከናወንበትን ልምድና ክህሎት እንዳዳበሩ አክለዋል።

ከቡኖ በደሌ የመጡት አቶ ደረጀ ረፌራም ስልጠናው ከዞናቸው ለመጡ ባለሙያዎች ስራውን በተያዘው ዕቅድ አፈፃፀምና አተገባበር ዙሪያ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉበትን ግንዛቤ የጨበጡበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዞናቸው 68 ሚሊዮን የሻይ ተክል ችግኝ ለማዘጋጀት ዕቅድ መያዙን የጠቀሱት አቶ ደረጀ ከስምንት ወረዳዎች መጥተው በስለጠናው የተሳተፉት ባለሙያዎች ትልቅ የአቅም ግንባታ ያገኙበት መሆኑንም አክለዋል።

የሻይ ልማት ግብርና በክልሉ መንግስት አቅጣጫ ተይዞባቸው ወደ ተግባር የተገባባቸው የግብርና ኢንሼቲቮች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም