የኢትዮ-ካናዳ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ፎረም በካናዳ ተካሄደ

121

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ካናዳ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ፎረም በካናዳ ቶሮንቶ ተካሄዷል።

በፎረሙ በርካታ የሁለቱም አገራት ባለሀብቶች የተሳተፉ ሲሆን በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ መምከራቸውን ኢዜአ ካናዳ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ፎረሙ የሁለትዮሽ ትብብርና የልምድ ልውውጥ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ባለሀብቶች በካናዳ የንግድ ገበያ እድሎችንና አጋርነቶች እንዲያገኙ በር የሚከፍት ነው ተብሏል።

የካናዳ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በግብርና፣ማኑፋክቸሪንግ እና ማዕድን ዘርፎች መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ፎረሙ እድል ይፈጥራል ነው ያለው ኤምባሲው በመረጃው።

በፎረሙ ከተገኙ የሁለቱ አገራት የንግድ ተቋማት መሪዎች ውስጥ የተወሰኑት በቀጣይ ይበልጥ ስለሚተዋወቁበት ሁኔታ ተከታታይ ውይይትና የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ መስማማታቸው ተጠቁሟል።

ፎረሙ በስኬት ተጠናቋል ያለው ኤምባሲው ሁነቱ የተሳካ እንዲሆን ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርቧል።

እ.አ.አ በ2021 የኢትጵያና ካናዳ የንግድ ልውውጥ መጠን እ.አ.አ 164 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ተጠቅሷል።

ከዚህ ውስጥ 112 ሚሊዮን ዶላሩ ካናዳ ወደ ኢትዮጵያ ከላከችው ምርቶች ያገኘችው ሲሆን 52 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ ካናዳ ከላከችው ምርቶች የተገኘ ገቢ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያና ካናዳ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እ.አ.አ በ1965 እንደተጀመረ መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም