ኢትዮጵያ በባለ ብዙ ወገን የትብብር ስርዓት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላት አገር ናት-አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በባለ ብዙ ወገን የትብብር ስርዓት ውስጥ ቁልፍ ሚና የምትጫወት አገር መሆኗን የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ።

78ተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ "ሰላም ፣ብልፅግና፣ ለውጥና ዘላቂነት" በሚል መሪ ሀሳብ በኒው ዮርክ መካሄዱን ቀጥሏል።

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከጉባኤው ጎን ለጎን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ዋና ፀሐፊው በተመድ የስደተኞች ኮሚሽን የስልጣን ዘመናቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ጥልቅ የሆነ የአጋርነት ስሜት እንደነበራቸው አውስተዋል።

ኢትዮጵያ ያሉባትን የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎችን ለመፍታት እያደረገች ባለው ጥረት ስኬታማ እንድትሆን ተመኝተዋል።

ጉቴሬዝ በስልጣን ዘመናቸው ተመድ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በባለ ብዙ ወገን የትብብር ስርዓት ቁልፍ ሚና ያላት አገር ናት ብለዋል ዋና ፀሐፊው።

አቶ ደመቀ ተመድ እና ዋና ፀሐፊው በግል ጥረታቸው ለኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ወቅቶች ያደረጉትን ድጋፍ አድንቀዋል።

አቶ ደመቀ ለአንቶኒዮ ጉቴሬዝ የሰላም ስምምነቱን ትግበራ አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

ተመድ የመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም ጥረቶችን እንዲሁም ሌሎች የሰብዓዊ ጉዳዮች ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም