የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግሮች በንግግር ለመፍታት ለሚደረገው ሀገራዊ ምክክር ስኬት የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል- የወጣት አደረጃጀት ኃላፊዎች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግሮች በንግግር ለመፍታት ለሚደረገው ሀገራዊ ምክክር ስኬት የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ የተለያዩ የወጣት አደረጃጀት ኃላፊዎች ገለፁ።

የኢትዮጵያን ሰላም በማጽናት በጥሩ መሠረት ላይ ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት በተለይም የወጣቶች ተሳትፎና እገዛ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል።

በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ደግሞ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል።


 

በመሆኑም ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የድርሻችንን እገዛና ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የወጣት አደረጃጀት ኃላፊዎች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና፤ ወጣቶች በሀገራዊ ምክክር ጉዳዮች ታዳሚ ብቻ ሳይሆኑ የአጀንዳው ባለቤት ሆነው መንቀሳቀስና ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ብሏል።

ሌላው የምክር ቤቱ አባል ኑር ሁሴን እና 'ዩዝ ካውንስሊንግ ሕብረት' የተሰኘው የወጣት አደረጃጀት ሊቀመንበር አብዲ መገርሳ፤ መሠረታዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የወጣቶች ተሳትፎና እገዛ ወሳኝ በመሆኑ ለዚሁ ስኬት መሥራት አለብን ነው ያለው።

ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት የድርሻችንን ለማበርከት ተዘጋጅተናል ሲሉ አረጋግጠዋል።

የመላው አፍሪካ ወጣቶች ድርጅት ምክትል ፕሬዝዳንት ወጣት መስፍን ደሴ፤ በሀገራዊ ምክክር መድረኮች የወጣቶች እገዛ፣ ተሳትፎና ትብብር በተጠናከረ መልኩ መቀጠል አለበት ብሏል።

የእንደራሴ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ብሩክ አስቻለው፤ ወጣቶች ለሀገራዊ ሰላምና አንድነት በትብብር የመሥራት ሀገራዊ ኃላፊነት አለባቸው ሲል ተናግሯል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የማኅበራዊ አንትሮፖሎጂ ምሁሩ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ፤ የሀገራዊ ምክክር ዓላማ ትናንትን ማከምና ነገን ማስተካከል በመሆኑ፤ ለዚሁ መልካም ተግባር መሳካት በተለይም የወጣቶች ተሳትፎ የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ሀገርን እየፈተኑ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ልማትን በማስቀጠል የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አተገባበር ገለልተኛና አካታችነትን መሠረት ያደረገ በመሆኑ በተለይም ወጣቶች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም