የግጭት ምክንያቶችን ለይቶ በማውጣትና እልባት በመስጠት ሰላምን ማጽናት ይገባል-የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ጋምቤላ፤ መስከረም 10/2016 (ኢዜአ)፡- የግጭት ምክንያቶችን ለይቶ በማውጣት እልባት በመስጠትና ሰላምን በማጽናት በኩል ሁሉም ዜጋ በአንድነትና በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሳሰበ። 

ኮሚሽኑ በአጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመምረጥ በጋምቤላ ከተማ ለሦስት ቀናት ያካሄደው መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፈን አርዓያ ባለመግባባት ምክንያት የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቀረትና ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ህዝቦች ችግር ሲገጥም በመነጋገርና በመመካከር ሊፈቱ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

በተለይም መሰረታዊ የግጭት መንሰኤ የሆኑ ምክንያቶችን ለይቶ በጋራ መፍታት ከተቻለ ሁሉም የሰላም አሸናፊ እንደሚሆን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

"የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ የግጭት መንስኤ የሆኑ ምክንያቶች ተለይተው እንዲፈቱ በማድረግ በህዝቦች መካከል መግባባትን መፍጠር ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

ይህንን ግብ ለማሳካት በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ከተባባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት በአጀንዳ ልየታ መድረክ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮችን ኮሚሽኑ እያስመረጠ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ከጋምቤላ ክልል ከሚገኙ 13 ወረዳዎችና ከጋምቤላ ከተማ መስተዳደር በአጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ 504 ተወካዮችን ማስመረጡንም ፕሮፌሰር መስፍን ተናግረዋል።

ከመድረኩ ታሳታፊዎች መካከል አቶ ዲድሙ አባላ በሰጡት አስተያየት እንደ ማህበረሰብ ተወካይነታቸው ኮሚሽኑ ለጀመረው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

"የሚያለያዩን ችግሮችን በማስወገድ፣ በመከባበርና በመደጋገፍ ሰላማችንን ልንጠበቅ ይገባል" ያሉት ደግሞ ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ሰይድ አሊ ናቸው።

ኮሚሽኑ በጋምቤላ ክልል ለሦስት ተከታተይ ቀናት ሲያካሄድ በቆየው መድረክ ከጋምቤላ ከተማ እና ከ13ቱ ወረዳዎች በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ 504 የማህበረሰብ ተወካዮችን በማስመረጥ ዛሬ ተጠናቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም