ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ  ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ስኬት ወጣቶች ግንባር ቀደም ሚና እንዲኖራቸው ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2016 (ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ  ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ስኬት ወጣቶች ግንባር ቀደም ሚና እንዲኖራቸው የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።

ዓለም አቀፉ የሰላም ቀን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የወጣት አደረጃጀቶችና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተገኙበት ተካሂዷል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ፤ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ግጭት ቀስቃሽ መልእክቶች፣ ፅንፈኝነት፣ ህገ ወጥነት፣ የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ከሰላም እጦት መንስኤዎች መካከል መሆናቸውን  ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የሰላም ዕጦት መንስኤዎችን በመለየት ችግሮችን ከምንጩ በማድረቅ ዘላቂ ሰላም መፍጠር ይገባል ብለዋል።

የትምህርትና የባህል ልውውጥን ማጠናከር፣ የዴሞክራሲ ባህልን ማዳበር፣ የስራ ዕድል ፈጠራን ማስፋትና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለዚህም ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ቤተሰብና ማህበረሰብ የድርሻቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

በሰላም ግንባታ ወጣቶች ቁልፍ ሚና ያላቸው ብቻ ሳይሆን የነገ ሀገር ተረካቢና መሪ በመሆናቸው ወጣቶች ላይ መስራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ነው ያሉት።

በመሆኑም ለኢትዮጵያ  ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ስኬት ወጣቶች ግንባር ቀደም ሚና እንዲኖራቸው ጠይቀዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ዶክተር ቶውፊቅ አብዱላሂ፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ግንባታ ወጣቶች ከፍተኛ ኃላፊነት ወስደው መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና፤ የዜጎችን የእርስ በርስ ግንኙነት ጥርጣሬ ላይ የሚጥል፣ የግጭትና ያለመግባባት መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን ማስወገድ የጋራ ኃላፊነታችን ነው ብሏል።

የሰላም ጉዳይ ከግለሰብ ስብዕና ጀምሮ እስከ ማኅበረሰብ ግንባታ የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ በመሆኑ በተለይም ወጣቶች ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ስኬት ግንባር ቀደም ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

በኢትዮጵያ እነዚህና ሌሎችም ለሰላም ማጣት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ለመሻት የሚያግዝ የወጣቶች ፎረም የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የመድረኩ ተሳታፊ ወጣቶች ከግጭት መንስኤዎች ከመራቅ ባለፈ በግጭት አፈታት ሂደቶች ላይ የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው ብለዋል።

በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ የሰላምና የልማት አጋር ሆነው መቆም ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

የዓለም የሰላም ቀን እ.ኤ.አ በ1981 በዓለም አቀፍ ደረጃ መከበር የጀመረ ሲሆን፤ የዘንድሮው "የወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ለዘላቂ ሰላም እና ለዓለም አቀፍ ግቦች" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም