ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ 350 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው -- የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን

ጅማ ፤መስከረም 10 / 2016 (ኢዜአ)፡-  በ2016 በጀት ዓመት 350 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በመላክ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ "የቡና ጥራት ለጋራ ብልፅግናችን" በሚል መሪ ቃል የቡና ምርት ጥራትን ማሳደግ የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ አካሂዷል።

በዚሁ ጊዜ የባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር እንዳሉት የቡና ልማትን በማሳደግ ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንድታገኝና አምራቹን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ለዚህም የግብይት ስርዓቱን ማዘመንና ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዲሁም እሴት በመጨመር የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት የዘርፉን ችግርች ለመፍታት ሲሰራ መቆየቱን ተናገረው በዚህም መልካም ውጤት መገኘቱን አብራርተዋል።

ዓምና ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ የተገኘ ሲሆን ይህም አበረታች ውጤት መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

በ2016 በጀት ዓመትም 350 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ገቢ ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የታቀደውን ግብ ለማሳካት በተለይም በጥራት ዙሪያ እየተስተዋለ ያለውን ችግር ለመፈታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

በ2015 በጀት ዓመት ከጥራት አንፃር ቡና አምራች በሆኑ የአገሪቷ የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች የቡና ጥራት ችግር በሰፊው መስተዋሉንም አስታውሰዋል።

ለዚህም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ የቡና ምርታማነትና ጥራትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ይረዳ ዘንድ "የቡና ጥራት ለጋራ ብልፅግናችን" በሚል መሪ ቃል የዘንድሮ ምርት ከመድረሱ በፊት ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊ እና የቡናና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ሀላፊ አቶ መሀመድሳኑ አሚን በበኩላቸው፣ በክልሉ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በቡና የተሸፈነ መሆኑን አንስተው ከዚህም ውስጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታሩ ምርት የሚሰጥ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በ2016 የምርት ዘመን ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመስብሰብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ መሀመድ 75 በመቶ ያህሉን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።

አምና የተገኘውን ተሞክሮ በማጠናከር ዘንድሮም ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ቡና ጥራቱ ተጠብቆ ለገበያ እንዲቀርብ ትኩረት ተደርጎ በመሰራቱ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የተናገሩት ደግሞ የሊሙ ኮሳ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ባህር ሀጂ ናቸው።

በመድረኩም የባለስልጣኑ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የስራ ሪፖርት አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን መሰል መድረክ በሌሎች ቡና አብቃይ አከባቢዎች እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም