ከ300 በላይ የአልሸባብ ታጣቂዎች ተደመሰሱ

አዲስ አበባ፤ መሰከረም 10/2016 (ኢዜአ):- ከ300 መቶ በላይ የአልሸባብ ታጣቂዎች ሲደመሰሱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አባላቱ መቁሰላቸውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።

በሶማሊያ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሠላም አሥከባሪ ሃይል ለመቀየር ተልዕኮ ወደ ሚፈፀምበት ቦታ በተንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ጠላት ቀድሞ ባገኘው መረጃ መሠረት ደፈጣ ይዞ ሠራዊታችን ላይ ጥቃት ለመሠንዘር የሞከረው አልሸባብ ባላሠበው መልኩ ክፉኛ መመታቱ ተገልጿል።

በተሳሳተ ስሌት የኢትዮጵያ ሠላም አሥከባሪ ቅይይር ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከረው የአልሸባብ ሃይል ከሶስት መቶ በላይ ታጣቂዎቹ ሲገደሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አባላቱም ቆስለዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱን ምት መቋቋም ያልቻለው አልሸባብ የሞቱ ታጣቂዎቹን አስክሬን እያንጠባጠበ ቁስለኞቹን በመያዝ ወደኋላ ለመፈርጠጥ ተገዷል ።

የኢትዮጵያ ሠራዊት የአልሸባብን ደፈጣ እያሥወገደና በየመንገዱ የጠመዱትን ፈንጂና መሠናክሉን እያስወገደ ከተልዕኮው ቦታ ሁዱር መድረስ ችሏል።


 

የአካባቢው ነዋሪዎችም ለመከላከያ ሠራዊታችን ምግብ እና ውሃ በማቅረብ ደስታቸውን እና ምስጋናቸውን ገልፀው፤ በሞራል ያላቸውን ድጋፍም አሳይተዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ከሥፍራው ደረሰኝ ባለው መረጃ የአልሸባብ ሃይል ሶስት ፈንጂ የጫኑ መኪናዎችን እና 12 ፈንጂ የታጠቁ ታጣቂዎቹን እንዲሁም ከአንድ ሺህ በላይ አሉኝ የሚላቸዉን አባላቱን ለጥፋት በደፈጣ አሰልፏል፡፡

የጥፋት ሃሳቡን ሳያሳካ በሠራዊታችን ክንድ መደምሰሱን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አልሸባብ በተለያዩ የምስራቁ የሀገራችን ክፍል ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን የአጥፍቶ መጥፋት ተግባራትን ለመፈፀም ሲሞክር የቆየ ቢሆንም የአሁኑ በታሪኩ ከፍተኛ የሠው ሃይል ያሳተፈበት እና ደፈጣዎች ይዞ ባላሠበው መንገድ የተመታበት መሆኑም ተገልጿል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም