የቀይ ባህር ቀጣና ሀገራት ሁለንተናዊ ትብብር በአካባቢው ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው - ሌተናል ጄነራል አለምሸት ደግፌ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2016 (ኢዜአ)፦የቀይ ባህር ቀጣና ሀገራት ሁለንተናዊ ትብብር በአካባቢው ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና ተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄነራል አለምሸት ደግፌ ገለጹ።

የቀይ ባህር ቀጣና ደኅንነትና ጂኦ-ፖለቲካል ሁኔታን በተመለከተ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትና በመከላከያ ዋር ኮሌጅ ትብብር የተዘጋጀ ውይይት ተካሂዷል።

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና ተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄነራል አለምሸት ደግፌ፤ የቀይ ባህር ቀጣና ስትራቴጂካዊ የንግድና የፖለቲካ ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል። 

ጂኦ-ፖለቲካ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታውም የጎላ በመሆኑ የበርካታ አገራትን ትኩረት ስለመሳቡ ተናግረዋል። 

በቀጣናው ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሽብርተኝነትና መሰል ችግሮች የጸጥታ ሥጋቶች ሆነው መቀጠላቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የቀይ ባህር ቀጣና ሀገራት አካባቢውን ከጸጥታ ስጋት በማውጣት የልማት መዳረሻ ለማድረግ በትብብር መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የአገራቱ የጋራ ትብብር ለቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።   

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስያና ፓስፊክ አገራት ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዶክተር ገበየሁ ጋንጋ፤ የቀይ ባህር ቀጣና አገራት በባህልና ኃይማኖት የተሳሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል። 

የቀይ ባህር ቀጣና በዓለም ካሉት ከፍተኛ የንግድ መስመሮች አንዱ በመሆኑ የአካባቢውን ጸጥታና ደኅንነት በጋራ በመጠበቅ ለጋራ ልማት መጠቀም ይገባል ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሳፍንት ተፈራ፤ የቀይ ባህር ቀጣና በኢኮኖሚ፣ ወታደራዊና መሰል ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የጸጥታ ሥጋቱ እየተወሳሰበ መጥቷል ብለዋል።

በመሆኑም ለቀጣናዊ ችግሮች ቀጣናዊ መፍትሔ ለመስጠት የአካባቢው አገራት ሁለንተናዊ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።  

በአሜሪካ የሰላም ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሉካ ኮል፤ አፍሪካ የውኃ ሀብቷን በአግባቡ ተጠቅማ ማልማት ካልቻለች በቀጣይ የከፋ ችግር ላይ ልትወድቅ ትችላለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አፍሪካ 90 በመቶ የውጭና ገቢ ንግዷን የምታሳልጠው በቀይ ባህር በኩል ቢሆንም በውኃ ሀብት አጠቃቀሟ "የባህር ላይ አይነ ስውር" ሆናለች ነው ያሉት፡፡

በአፍሪካ የባህር ዳርቻ ያላቸው ሀገራት ከዓለም ሀገራት ጋር ሲነፃፀሩ ዝቅተኛ የውኃ ሀብት ተጠቃሚ መሆናቸውን ማሪታይም ደህንነት ኢንዴክስ መረጃን ዋቢ በማድረግ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም አፍሪካውያን የቀይ ባህርን ጨምሮ የውኃ ሀብታቸውን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም