ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ የማስተላለፍ ግዴታ ላይ ያደረገው ማሻሻያ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው-የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ የማስተላለፍ ግዴታ ላይ ያደረገው ማሻሻያ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው-የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ የማስተላለፍ ግዴታ ላይ ያደረገው ማሻሻያ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለፀ።
ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ዓላማ ያደረጉ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የባንኩ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ነሐሴ 05 ቀን 2015 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።
ከፖሊሲ ማሻሻያዎቹ አንዱ በቁልፍ የወጪ ንግድ ዘርፎች በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ላኪዎችን ለማበረታታት የውጭ ምንዛሪን የማስተላለፍ ግዴታ ከ70/30 ወደ 50/50 እንዲሻሻል መደረጉ ነው።
በዚህም መሰረት የሸቀጦች እና የአገልግሎት ላኪዎች ካፈሩት የውጭ ምንዛሪ ገቢ 50 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ፣ 10 በመቶውን ለባንካቸው በማስተላለፍ ቀሪውን በራሳቸው የባንክ ሂሳብ እንዲያስገቡ ተወስኗል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ከኢዜአ ጋርባደረጉት ቆይታ፤ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፍ ግዴታ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ለአምራች ዘርፉ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አምራች ኢንዱስትሪው በአብዛኛው ግብዓት ከውጭ የሚያስገባ በመሆኑ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲፈተን መቆየቱን አውስተዋል።
የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ የማስተላለፍ ግዴታን ከ70/30 ወደ 50/50 እንዲሻሻል ማድረጉ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ባንኩ የወሰደው እርምጃ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደ ማነቆ ለሚነሳው ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር እልባት እንደሚሰጥ በመጥቀስ።
ማሻሻያው አምራቾችን የሚያበረታታና የዘርፉን ምርታማነት ለማሻሻል አቅም እንደሚፈጥርም ነው አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ያብራሩት።