ምስራቅ ወለጋ ዞንን ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ እንደሚሰራ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ምስራቅ ወለጋ ዞንን ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ እንደሚሰራ ተገለጸ
ነቀምቴ ፤ መስከረም 10/2016(ኢዜአ) :-ምስራቅ ወለጋ ዞን ባለው ተፈጥሯዊ ሀብትና ምቹ መልክዓ ምድር ልክ ለኢንቨስትመንት ልማት ምቹ ለማድረግ እንደሚሰራ ተገለጸ።
የምስራቅ ወለጋ ዞንና የነቀምቴ ከተማ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤቶች ከባለሀብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት ፎረም አካሄደዋል።
በፎረሙ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መርጋ ቀነአ እንዳሉት ምስራቅ ወለጋ እና ነቀምቴ ከተማ የተስማሚ አየር ንብረትና የበርካታ ተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆናቸውን አንስተዋል።
ይኸንን ሀብት ወደ ልማት መቀየር እንደሚገባ ያነሱት አቶ መርጋ፤ ዞኑ በተለይም ባለው ተፈጥሯዊ ሀብትና መልክዓ ምድር ልክ ለኢንቨስትመንት ልማት ምቹ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህም የዘርፉ ሴክተር መስሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡና የባለሀብቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አንስተው ለዚህም ቢሮው አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
በተለይም ባለሀብቶች መጥተው እንዲሰሩ ዞኑ በሰላምና ጸጥታው እንዲሁም አሰራሮችና መዋቅሮችን ምቹ በማድረግ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት እንደሚገባው አሳስበዋል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ለማ በበኩላቸው ባለሀብቶች አዋጭ የሥራ ዘርፎችን መርጠው እንዲሰማሩ ዞኑ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት እንደ ዞኑ 1ሺህ 169 አዳዲስ ኢንቨስተሮችን ወደ ሥራ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው እስካሁን ባለው ሂደትም 68 ኢንቨስተሮች ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልፀዋል።
በዞንና በነቀምቴ ከተማ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የመጡ ባለሀብቶች እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የነቀምቴ ከተማ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበበ ኦላና ናቸው።
ዞኑም ሆነ ነቀምቴ ከተማ አልፎ አልፎ የጸጥታ ችግር እንደሚታይባቸው አንስተው፣ ከተማ አስተዳደሩም ሆነ ዞኑ ከማህበረሰቡና ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ከፎረሙ ተሳታፊዎች መካከል በጊዳ አያና በኢንተርፕራይዝ ሥራ ላይ የሚገኙት አቶ መርጋ አበበ የተዘጋጀው መድረክ አበረታች መሆኑን በመግለፅ ከጸጥታ እና ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ያለውን እጥረት መቅረፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዞኑ ያለውን ምቹ የአየር ንብረት እና የሰው ሃይል በመጠቀም ከዞኑ ባለፈም ሀገሪቷን መደገፍ እንደሚቻልም አንስተዋል።
በዘይት ምርት ላይ ተሰማርተው የሚገኙት አቶ ኛሬ ጂሬኛ በበኩላቸው በመንግሥት አካላት በኩል ያለው የሥራ ድጋፍና ማበረታቻ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል።
በኢንቨስትመንት ሥራ ውስጥ የተለያዩ አካላት ተሳትፎ ለሚመዘገበው ውጤት መሰረት ነው ያሉት አቶ ኛሬ፤ አንድ ሀገር ማደግ እና መለወጥ የምትችለው በግል ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦችን በማበረታታት ነው ብለዋል።
የኢንቨስትመንት ሥራቸውን ለማስፋት ሀሳብ እንዳላቸው ገልጸው፤ ለዚህም ዞኑ በተለይም አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር ቅድሚያ በመስጠት ሊሰራበት እንደሚገባ ጠይቀዋል።
የእርሻ ስራ፣ የማር ምርት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ ቡና፣ ቆዳና ሌጦ፣ የእንስሳት እርባታ፣ የማዕድን ልማት፣ ሆቴል እና ቱሪዝም መስኮች ደግሞ በዞኑ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች መሆናቸው በመድረኩ ላይ ተገልጿል።