የውሃ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ማደራጀት ሥራ እየተከናወነ ነው- ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ማደራጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ ገለጹ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ፤ የውሃ ሃብት አጠቃቀምና በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ማደራጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

የመረጃ ቴክኖሎጂው አጠቃላይ የውሃ ሃብትን ለማስተዳደር፣ የሃብቱን መገኛ አካባቢዎች በመለየት ለማልማትና የአጠቃቀም ስልቶችን የሚያመላክት መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት በተደራጀና ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት በመሰነድ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።

የውሃ ሃብት መረጃን በዘመናዊ የመረጃ ቋት በማስቀመጥ ከአካባቢው አገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጠናከርና የውሃ ዲፕሎማሲ (ሃይድሮ ዲፕሎማሲን) ለመገንባት ጠቃሚ መሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት በምርምር የተደገፈና በተጨባጭ መረጃ የተደራጀ በማድረግ ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የውሃ ሃብትን በዘለቄታ በመጠቀም ሁለንተናዊ ልማትና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የውሃ ሃብትን በእውቀትና ምርምር ታግዞ ጥቅም ላይ ለማዋል የተቀናጀ ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ የሁሉም ጥረት እንዲታከልበት ጠይቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም