የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከማይክሮሶፍት ኩባንያ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2016 (ኢዜአ)፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 78ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ከማይክሮሶፍት ኩባንያ የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ ማይክሮሶፍትና ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ነው።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስለሚገኘው የቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እንዲሁም ወጣቶችን በዲጂታል እውቀት ለማበልጸግ እየተደረገ ስለሚገኘው ጥረት ለሃላፊዎቹ ገለጻ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለማሳደግ እየሰራች ስለምትገኘው ስራ ያብራሩ ሲሆን ይህም ከኩባንያው ጋር በትብብር የሚሰራበት አንዱ ዘርፍ እንዲሚሆን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል መሰረተ-ልማትን ለማስፋት በተለይ በክላውድ አገልግሎት፣ ዳታ ማእከልና ሌሎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ውጤቶች ከማይክሮሶፍት ጋር መስራት እንደምትፈልግም ገልጸዋል።

በቴክኖሎጂ የስራ ፈጠራ ላይ ጀማሪዎችን ለማበረታታት ኩባንያው በገንዘብ፣ በስልጠናና አስፈላጊ ግብአቶችን በማቅረብ ኢትዮጵያን ሊያግዝ ስለሚችልባቸው ጉዳዮች ገለጻ አድርገዋል።

የማይክሮሶፍት ኩባንያ የስራ ሃላፊዎች በበኩላቸው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ለጤና፣ ለግብርና እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአፍሪካ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ፕሮግራሙን ለማስፋፋት ኢትዮጵያን እንደ አማራጭ ለመጠቀም ፍላጎት እንዳለውም ሃላፊዎቹ ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም