ቀጥታ፡

የሀገሪቱን ህግ አክብረው የማይሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2016 (ኢዜአ)፦  የሀገሪቱን ህግ አክብረው የማይሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ገለጸ።

በ2015 በጀት ዓመት ከህግና አሰራር ጥሰት ጋር በተያያዘ አንድ ድርጅት የህግ ፈቃዱ የተሰረዘ ሲሆን ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መኖራቸውም ተገልጿል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግን አክብረውና መርህን ተከትለው እንዲሰሩ ተገቢ ድጋፍና ክትትል እያደረገ ይገኛል።

በመስክ ምልከታ ጭምር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ሁኔታ እንደሚከታተል አንስተው ጥቆማዎችን በመቀበልና በማጣራት የእርምት እርምጃ እየተወሰደ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከጥቅል በጀታቸው 20 በመቶውን ለተቋማዊ አስተዳደር፣ 80 በመቶውን ለዓላማ ማስፈጸሚያ ማዋል ያለባቸው ቢሆንም፤  ይህንን ተፈጻሚ የማያደርጉና ክፍተት ያሳዩ ድርጅቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

የተቋማዊ ዓላማ ማስፈጸሚያ ገንዘብን ለግል ጥቅም በማዋል ህገወጥ ተግባር የፈጸመ አንድ ድርጅት የስራ ፈቃዱ መሰረዙን ገልጸው፤ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸውና ማጣራት እየተደረገባቸው የሚገኙ ድርጅቶችም መኖራቸውን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ቁጥጥር ከተደረገባቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል 647 በአረንጓዴ፣ 134 በቢጫ፣ 396 በቀይ እና 119 ድርጅቶች በጥቁር መዝገብ ዝርዝር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ከቀላል እስከ ከባድ የማስተካከያ ስራ እንዲያካሂዱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ነው ያሉት።

በአረንጓዴ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት የተሻለ ስራ ያከናወኑና ሊበረታቱ የሚገቡ፤ በቢጫ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ደግሞ ጥቂት ስህተቶች ያሉባቸውና መጠነኛ ማስተካከያዎችን ማድረግ የሚጠበቅባቸው እንደሆኑም አንስተዋል።

በቀይና በጥቁር መዝገብ ደረጃ የሚገኙ ድርጅቶች ውስብስብ ችግሮች ያሉባቸው በመሆናቸው አፋጣኝ የእርምት እርምጃ መውሰድ እንደሚገባቸው ጠቅሰው፤ ማስተካከያ የማያደርጉ ከሆነ ግን ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ ይሰራል ብለዋል።

የሰው ኃይል አስተዳደር፣ የግዥና ፋይናንስ አስተዳደር ህግን ጨምሮ ተቋማዊ አሰራር የሌላቸው፣ በእቅድ መሰረት የማይሰሩና የሚያገኙትን የድጋፍ ገንዘብ ለተጠቃሚዎች በአግባቡ የማያውሉ ድርጅቶች እንዳሉ በቁጥጥር ስራ መረጋገጡን አስረድተዋል። 

እነዚህ ድርጅቶች የአሰራር ክፍተታቸውን እንዲያርሙ ማስጠንቀቂያ  እንደተሰጣቸው ጠቅሰው፤ ማስተካከያ በማያደርጉት ላይ የህግ ፈቃዳቸውን እስከመሰረዝ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አሳስበዋል።

በ2016 በጀት ዓመት የሲቪል ማህበራትን ምቹ የስራ ምህዳር ከማስፋት ባሻገር የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም አንዳንድ ድርጅቶች የማስተካከያ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ባለስልጣኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም