በቀይ ባህር አካባቢ የሚስተዋሉ የጸጥታ ሥጋቶችን በማስወገድ የቀጣናውን ደኅንነት ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት ይገባል - ሌተናል ጄኔራል አለምሸት ደግፌ - ኢዜአ አማርኛ
በቀይ ባህር አካባቢ የሚስተዋሉ የጸጥታ ሥጋቶችን በማስወገድ የቀጣናውን ደኅንነት ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት ይገባል - ሌተናል ጄኔራል አለምሸት ደግፌ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2016 (ኢዜአ)፦ በቀይ ባህር አካባቢ የሚስተዋሉ የጸጥታ ሥጋቶችን በማስወገድ የቀጣናውን ደኅንነት ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት እንደሚገባ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና ተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አለምሸት ደግፌ ገለጹ።
የቀይ ባህር ቀጣና ደኅንነትና ጂኦ-ፖለቲካል ሁኔታን በተመለከተ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትና በኢፌዴሪ መከላከያ ዋር ኮሌጅ ትብብር የተዘጋጀ ውይይት እየተካሄደ ነው።
የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና ተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አለምሸት ደግፌ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የቀይ ባህር ቀጣና ስትራቴጂካዊ የንግድና የፖለቲካ ማዕከል ነው።
የቀይ ባህር ቀጣና ጂኦ-ፖለቲካ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸው ይህም የበርካታ አገራትን ትኩረት መሳቡን ገልጸዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን ቀጣናው ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሽብርተኝነትና መሰል የጸጥታ ሥጋቶችም የሚስተዋሉበት ነው ብለዋል።
በመሆኑም አሁን ላይ የቀጣናው የደኅንነት ሥጋት ከፍ እያለ መምጣቱን ነው ያስረዱት።
በመሆኑ እነዚህን ችግሮች ለመከላከል የቀጣናውን አገራት ትብብር ይፈልጋል ያሉት ሌተናል ጄኔራል አለምሸት የአገራቱ የጋራ ትብብር ለቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስያና ፓስፊክ አገራት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዶክተር ገበየሁ ጋንጋ፤ የቀይ ባህር ቀጣና አገራት በባህልና ኃይማኖት የተሳሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።
የቀይ ባህር ቀጣና በዓለም ካሉት ከፍተኛ የንግድ መስመሮች አንዱ በመሆኑ የአካባቢውን ጸጥታና ደኅንነት በጋራ በመጠበቅ ለጋራ ልማት ማዋል ይገባል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሳፍንት ተፈራ፤ የቀይ ባህር ቀጣና በኢኮኖሚ፣ ወታደራዊና መሰል ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የጸጥታ ሥጋቱ እየተወሳሰበ መጥቷል ብለዋል።
በመሆኑም ለቀጣናዊ ችግሮች ቀጣናዊ መፍትሔ ለመስጠት የአካባቢው አገራት ሁለንተናዊ ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው ነው ምክረ-ኃሳባቸውን የሰጡት።