የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድራቸውን ተጽዕኖዎች ለመከላከል ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር ያስፈልጋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድራቸውን ተጽዕኖዎች ለመከላከል ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር ያስፈልጋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2016 (ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድራቸውን ተጽዕኖዎች ለመከላከል ዓለም አቀፍ ቅንጅታዊ ትብብርን ማጎልበት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ “ሰላም፣ብልጽግና፣ለውጥና ዘላቂነት” በሚል መሪ ሀሳብ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን በተካሄደ የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከተ ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።
አቶ ደመቀ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከፍተኛ የሚባል መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በመርሐ-ግብሩ እስከ አሁን ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውንና የተለያዩ ውጤቶች እየተገኙበት መሆኑንም አመልክተዋል።
የአደጋዎች ስፋት፣ መጠንና የሚከሰቱበት የጊዜ ገደብ ታሳቢ በማድረግ ኢትዮጵያ ፖሊሲዎቿን በመለወጥ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት የማጠናከር ስራ በማከናወን ላይ ነች ብለዋል።
በዚህ ረገድም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉትዬሬዝ “ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለሁሉም” በሚል የጀመሩትን ኢኒሺዬቲቭ አቶ ደመቀ አድንቀዋል።
ዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊውን ቅንጅትና ትስስር በመፍጠር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው ያብራሩት።
በአገር፣ በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ውጤታማ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ለመገንባት አስፈላጊው የፋይናንስ ድጋፍ እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።