ለኢትዮጵያ  ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ስኬት ወጣቶች ግንባር ቀደም ሚና እንዲኖራቸው ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2016 (ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ስኬት ወጣቶች ግንባር ቀደም ሚና እንዲኖራቸው የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።

ዓለም አቀፉ የሰላም ቀን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተለያዩ መርሃ-ግብሮች እየተከበረ ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የወጣት አደረጃጀቶችና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና፤ የሰላም ጉዳይ መሠረታዊና ሁሉንም የሚመለከት የጋራ ጉዳያችን ነው ብሏል።

በየትኛውም አጋጣሚ ሰላም ከሌለ ሁሉንም በመጉዳት ለሕይወት ማጣት፣ የአካል ጉዳትና የስነ-ልቦና ጫና የሚዳርግ በመሆኑ፤ ሰላምን አጥብቀን መሻትና ለዚያም መሥራት አለብን ነው ያለው።

የዜጎችን የእርስ በርስ ግንኙነት ጥርጣሬ ላይ የሚጥል፣ የግጭትና ያለመግባባት መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን ማስወገድ የጋራ ኃላፊነታችን ሊሆን ይገባል ነው ያለው።

በተለይም ወጣቶች ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ስኬት ግንባር ቀደም ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

የሰላም ጉዳይ ከግለሰብ ስብዕና ጀምሮ እስከ ማኅበረሰብ ግንባታ የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑንም አብራርቷል።

በማይገባ ነገር ላይ እርስ በርስ መፈራረጅ፣ የጦርነት ቅስቀሳ፣ ዘረኝነትና ዋልታ ረገጥ እሳቤ ሁሉንም የሚጎዳ የጋራ ችግር መሆኑንም አንስቷል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ እነዚህና ሌሎችም ለሰላም ማጣት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ለመሻት የሚያግዝ የወጣቶች ፎረም የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሷል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ዶክተር ቶውፊቅ አብዱላሂ፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ግንባታ ወጣቶች ትልቅ ኃላፊነት ወስደው መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የዓለም የሰላም ቀን እ.ኤ.አ በ1981 በዓለም አቀፍ ደረጃ መከበር የጀመረ ሲሆን፤ የዘንድሮው "የወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ለዘላቂ ሰላም እና ለዓለም አቀፍ ግቦች" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ይሆናል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም