ለቡና ምርታማነትና ጥራት መረጋጋጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው- ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
ለቡና ምርታማነትና ጥራት መረጋጋጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው- ባለስልጣኑ
ጅማ፤ መስከረም 10/ 2016 (ኢዜአ)፡- ለቡና ምርታማነትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ያጎለበተ ጥራት መረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጸ።
"የቡና ጥራት ለጋራ ብልፅግናችን" በሚል መሪ ሀሳብ ባለስልጣኑ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመተባባር ያዘጋጀው የቡና ምርት ጥራትን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያግዝ የንቅናቄ መድረክ በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የባለሥልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳህለማሪያም ገብረመድህን በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት ፤ የቡናን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በስፋት እየተሰራ ነው።
ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ያጎለበተ የቡና ጥራት ለማረጋገጥም ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው አመልክተው፤
ለዚህ የሚያግዝ የንቅናቄ መድረክ በጅማ ከተማ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
መድረኩ የቡና ምርታማነትንና ጥራትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንዲያግዝ ታስቦ እንደተዘጋጀ አስረድተዋል።
በቀጣይ ተመሳሳይ የንቅናቄ መድረኮች በሌሎች ቡና አምራች ክልሎችም እንደሚደረግ አቶ ሳህለማሪያም አስታውቀዋል።
ባለፈው ዓመት "የቡና ምርት ጥራት ለምርታማነት እድገት" በሚል የመጀመሪያው ዙር ንቅናቄ ተደርጎ የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
በመድረኩም የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር፣ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ መሐመድሳኒ አሚን፣ የጅማ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ የሱፍ ሻረውን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮች ተገኝተዋል።