አየር መንገዱ ለኤጀንሲው 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚገመት የመማሪያ ቁሳቁስና ለምገባ ፕሮግራም የሚውል የገንዘብ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ ለኤጀንሲው 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚገመት የመማሪያ ቁሳቁስና ለምገባ ፕሮግራም የሚውል የገንዘብ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 9/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚገመት የመማሪያ ቁሳቁስ እና ለምገባ ፕሮግራም የሚውል የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለምገባ ፕሮግራም የ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብርና ቀሪው 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚያወጣ 48 ሺህ የመማሪያ ደብተር ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ አስረክቧል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ ከተለያዩ ወገኖች ድጋፍ በማሰባሰብ በመዲናዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ እና የመማሪያ ቁሳቁስ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ ሰው ተኮር ተግባራትን ያከናውናል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም በዛሬው ዕለት የ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት 48 ሺህ የመማሪያ ደብተር ለኤጀንሲው አስረክቧል።
በአየር መንገዱ የሰው ኃብት ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ዘነበወርቅ ገብረጻዲቅ እንዳሉት፤ የደብተር ድጋፉ በለሚኩራ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ጨፌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚውል ነው።
የደብተር ድጋፉ ለ4 ሺህ ተማሪዎች ተደራሽ እንደሚሆንም ገልፀዋል።
ከዚህ ባሻገር አየር መንገዱ በዚሁ ትምህርት ቤት ለሚገኙ 970 የመዋዕለ ሕፃናት ተማሪዎች የአንድ ወሰነ- ትምህርት የምገባ ፕሮግራም ወጪ የሚሸፍን የ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ስንታየሁ ማሞ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የምግብ እና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ በትውልዱ ላይ ትልቅ አሻራውን ማሳረፉን ተናግረዋል።
ድጋፉ በተማሪዎች የትምህርት ጥራት ላይ ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
ሌሎች ተቋማት፣ ባለሀብቶች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ይህን አርዓያነት በመከተል ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።