ቀጥታ፡

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከወጪ ንግድ በተጨማሪ ገቢ ምርቶችን በመተካት ለመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው

አዳማ ፤ መስከረም 9/2016 (ኢዜአ)፦የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከወጪ ንግድ በተጨማሪ ገቢ ምርቶችን በመተካት ለመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር የበኩሉን ሚና  እየተወጣ መሆኑን የፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት አበበ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከሚያስተዳድራቸው 13 ፓርኮች መካከል የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንዱ ነው። 


 

ፓርኩ 365 ሄክታር ላይ ያረፈ ሲሆን፤ የጃፓን ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ኖርዌይ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እንዲሁም የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ተሰማርተውበታል፡፡

ኩባንያዎቹ በዋናነት  በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ፣ በቀለም እንዲሁም  በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ናቸው፡፡

የፓርኩ ስራ አስኪያጅ ጉልላት አበበ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ 19 የማምረቻ ሼዶች ወደ ምርት ገብተዋል፡፡

በዚህም 14 የሚሆኑ የአገር ውስጥ እና የውጭ ኩባንያዎች በፓርኩ ወስጥ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፓርኩ ውስጥ እየሰሩ ያሉ ኩባንያዎች በአገር ውስጥ ካሉ ድርጅቶች ጋር 300 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የንግድ ትስስር መፍጠራቸውን ገልጸዋል።


 

በተጨማሪም ፓርኩ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን ባለው ሂደትም 600 ሚሊዮን ብር ይወጣባቸው የነበሩ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ 

የአምራች ዘርፉ ሀብት በመፍጠር ዙሪያ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ወደ አምራች ዘርፉ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ፓርኩ ለ8 ሺህ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉንም ነው የጠቀሱት፡፡  

የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ከሚያደርገው አስተዋፅኦ ባሻገር አገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግር እገዛ እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም