ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከኩባ ጋር ያላትን የትብብር አድማስ በማስፋት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር እየሰራች ነው - አምባሳደር ገነት ተሾመ  

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 9/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከኩባ ጋር ያላትን የትብብር አድማስ በማስፋት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን በኩባ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ ገለጹ። 

አምባሳደር ገነት ሁለቱ አገራት ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ወዳጅነትና ትብብር እንዳላቸው ገልጸው ኩባ በተለይም ለኢትዮጵያ በርካታ ድጋፎችን ማድረጓን ጠቁመዋል።  

የኩባ ወታደሮች ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መስዋዕትነት መክፈላቸውን አስታውሰው ይህ ውለታ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚረሳ አይደለም ብለዋል።

ኩባ በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የትምህርት እድል መስጠቷንም ጠቁመዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን የኩባ የሕክምና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ለሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች የትምህርትና የሥልጠና ድጋፍ እየሰጡ መሆኑን አመልክተዋል።

ኩባ በግብርና፣ በውኃ ኃብት ልማት፣ በመስኖ፣ አካባቢ ጥበቃና በተለያዩ መስኮች ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል እንደምትሻም ገልጸዋል።

የሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ሳይንስና ቴክኖሎጂን ጨምሮ በተለያዩ የትብብር መስኮች አጋርነቱን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።     

በቅርቡ በኩባ መዲና ሃቫና በተካሄደው የቡድን 77 እና ቻይና ጉባኤ፤ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን መሳተፉ ይታወሳል። 

ከጉባኤው ጎን ለጎን አቶ ደመቀ ከኩባ ፕሬዝዳንት ሚጉዌል ቤርሙዴዝ ፈርናንዴዝና ከሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የሁለቱን አገራት አጋርነትን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ  መክረዋል። 

ኢትዮጵያና ኩባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1975 ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም