የመኔ ሸድዬ ባሮ - የጠንካራ የስራ ባህል፣ የአብሮነትና የሰላም ተምሳሌት

በሽመልስ ጌታነህ (ኢዜአ)

የመኔ ሸድዬ ባሮ የካፈቾ ብሄር ከአሮጌው ዘመን ወደ አዲሱ የሚሸጋገሩበት፣ የአዲስ ዘመን ብስራትና የዘመን መለወጫ በዓል ነው። በዓሉ የጠንካራ የስራ ባህል፣ የአብሮነትና የሰላም ተምሳሌት በዓል እንደሆነ ይነገርለታል። በዚህም የካፋ ብሄር ለዘመናት የገነባውና ጠንካራ የስራ ባህል፤ ተፈጥሮን የመጠበቅና የመንከባከብ እንዲሁም ከተለያዩ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ተቻችሎና ተፈቃቅሮ የሚኖር ሲሆን ቱባ ዕሴቱ ዛሬም ላለው ትውልድ መሰረት መሆኑን ያምኑበታል። የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩት ከሆነ የካፋ ህዝብ ጠንካራ ንጉሳዊ ሥርዓት የነበረው፤ የታሪክና የቱባ ባህል ባለቤትም ነው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የታሪክ ባለሙያና የሀገር ሽማግሌ አቶ አሰፋ ገብረማሪያም የካፈቾ ብሄር ዘመን መለወጫ  በሃገሬው አጠራር ''የመኔ ሸድዬ ባሮ'' በዓል የካፋ ህዝብ ከሚያከብራቸው በርካታ በዓላት ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ። በዓሉ ያለውን ግዝፈት ሲያመለክቱ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ፀሐፍት ጭምር “ታላቁ በዓል ወይም (ግሬት ፌስቲቫል)” ተብሎ እንደሚጠራም ተናግረዋል።

በዓሉ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዳራ ያለው ሲሆን ከጥንት ካፋ ንጉስ ጀምሮ በየአመቱ በድምቀት የሚከበር በዓል እንደሆነም ጠቁመዋል። የካፋ ህዝብ ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከጎሳ መሪነት አንስቶ ጠንካራ የመንግስት መዋቅር የነበረው ታላቅ ህዝብ እንደሆነ ያነሱት አቶ አሰፋ፣ በዚህም በዓሉ በዘመኑ የነበሩ መንግስታት በዓል እንደነበረም አብራርተዋል።

ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም የሚገመገምበት ጥሩ የሠራና የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገበ  የሚሸለምበትና ለበለጠ ሥልጣን የሚታጭበት፤ ሰነፉ ደግሞ የሚወቀስበትና ስልጣኑ የሚነጠቅበት ታላቅ በዓልም ነው ብለዋል። ይህም በብሄሩ ዘንድ ለዘመናት የተሻገረ የጠንካራ የሥራ ባህል ግንባታ መሰረት ሆኖ የቆየ መሆኑን አንስተዋል። ይህ ሁሉ ሲከናወን በማህበረሰባዊ የህግ ተገዥነት መሰረት መሆኑ የተለየ እንደሚያደርገው ገልጸው ከሁሉ በፊት ሰላምን በማስቀደም መንግስትንና ህግን ማክበር እንዲሁም ህግ የሚመራው ህዝብ የበላይ መሆኑን አመላካች ሥርዓት መሆኑን አንስተዋል።


በዓሉ ከአዝመራ ጋር የተያያዘ የዘመን አቆጣጠርን ተከትሎ  እንደሚከበርም የታሪክ ባለሙያው አቶ አሰፋ ይገልጻሉ።  እንደ ታሪክ ተመራማሪው ገለጻ የካፋ ህዝብ አብዛኛው አርሶ አደር አልፎም አርብቶ አደር ሲሆን ለአዝመራ የተለየ ትኩረት ይሰጣል፤  በዓሉ ሊከበር 77 ቀናት ሲቀሩት ህዝቡ የአዲስ ዘመን መለወጫ ብሎ ሃምሌ አንድ  አዝመራውን እንደሚጀምርም ጠቁመዋል። የአዝመራ ወቅት ሊገባደድ  25 ቀናት ሲቀሩት (ከሼ ዋጦ) ብሎ አዝመራውን ያጠናቅቃል። ወቅቱም ጨለማው አልፎ በብርሃን የሚተካበት፤ ክረምቱ  ለበጋ  ቦታውን የሚለቅበት በመሆኑ አዲስ አመት መድረሱን ያሳውቃል።

ያን ጊዜ በጥንት የካፋ ምክርቤት ከሚገኙ ሰባት የሚክረቾ አባላት ውስጥ አንዱ የሆነው አዲዬ ራሾ ፤ የንጉሱ መቀመጫ በሆነው ቦንጌ ሸምበቶ በዓሉን ለማክበር ከየአቅጣጫው ለሚመጣው ህዝብ መንገዶችን በማፅዳት እና ለወንዞች ድልድይ በማበጀት በዓሉ መድረሱን ያበስራል። ያን ጊዜ በዓሉን ለማክበር ህዝብ ከያለበት አቅጣጫ ወደ ቦንጌ ሸምበቶ ይተማል። ህዝቡ በቦንጌ ሸምበቶ ከተሰበሰበ በኋላም ንጉሱ በተገኙበት የእያንዳንዱ ወራፌ ራሾ ሥራ ይገመገማል፤ ጥሩ ሥራ የሠራ ጠንካራ መሪ ይሸለማል፤ ለበለጠ ስልጣንም ይታጫል፤ ሀላፊነቱን በተገቢ ሁኔታ ያልተወጣው ደግሞ ይመከራል፣ ይወቀሳል አልፎም ስልጣኑን ይነጠቃል። ዛሬም ሀገራችን ይህ አይነቱን ጠንካራ የሥራ ባህል  አብዝታ ትሻለች፤ እንዲህ አይነት ሀገር በቀል ዕውቀቶች ትውልዱን በጠንካራ ሥነ-ምግባርና የሥራ ባህል ለመገንባት ትልቅ ድርሻ አላቸው።


በተጨማሪም በዓሉ ቅሬታዎችን ለመፍታትና ሰላምን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ፤ ቂምና ጥላቻን ይዞ ወደ ንጉሱ ፊት መቆምም ይሁን ወደ አዲሱ ዓመት መሻገር ነውር ተደርጎ የሚወሰድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ በዓሉ ከመምጣቱ አስቀድሞም ይሁን በበዓሉ ወቅት የተጣላ ይታረቃል፤ ጥላቻም በፍቅር ይተካል ብለዋል የታሪክ ተመራማሪው። እንዲህ አይነቱ ሀገር በቀል ዕውቀት ጠንካራ ባህል ለመገንባት፤ ቅራኔዎችን በሰላም ለመፍታትና ማህበራዊ ግኑኝነቶችን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ ስላላቸው በትምህርት ሥርዓት ውስጥ አካቶ ማስተማርና ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ሲሉም ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

ሌላኛው የሀገር ሽማግሌና የካፋ፣ጫራ እና ናኦ የባህል ምክርቤት አባል አቶ ፀጋዬ ገብረማሪያም እንደሚሉት የካፋቾ ''የመኔ ሸድዬ ባሮ'' በዓል ማህበራዊ ግንኙነትን በማጠናከሩ ረገድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በዓል ነው። ምክንያቱ ደግሞ፣ በዓሉን ለማክበር በአካባቢው ያሉ፣ በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ እንዲሁም ባህር ማዶ የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆች የሚሰበሰቡበት ታላቅ በዓል ስለሆነ ነው ብለዋል።

በዚህም የተራረቀ የሚገናኝበት፤ የተጠፋፋ የሚጠያየቅበት ሲሆን ህዝቡ በአንድ ላይ ተሰብስቦ በንጉሱ ተመርቆ፣ በልቶ ጠጥቶ እንዲሁም ተጫውቶ ወደ ቀጣዩ አመት በደስታና በታላቅ ተስፋ የሚሸጋገርበት እንደሆነም አብራርተዋል። ይህ ባህል በተለያዩ ምክንያቶች ከ120 ዓመታት በላይ ሳይከበር እንደቆየ የገለፁት አቶ ፀጋዬ ገብረማሪያም ዳግም መከበር ከጀመረበት ስምንት ዓመታት ወዲህ የነበረውን ታሪክና ባህል በሚያስቀጥል መልኩ በየዓመት በድምቀት እየተከበረ መሆኑንም አንስተዋል።
ወጣቱ ትውልድ ባህሉንና ታሪኩን አውቆ እንዲኖርና እንዲያስቀጥል ግንዛቤ የመፍጠርና የማስተማር ሥራ በሰፊው እየተሠራ እንደሆነም ገልፀዋል። ከዚህ ባለፈም ባህሉንና ታሪኩን ለማስቀጠል የባህል ምክር ቤቱ የወረዳ የባህል ምክር ቤቶችን የማጠናከር፣ ታሪካዊ ቅርሶችን የመሰብሰብና የማደራጀት ሥራ እየሠራ ነውም ብለዋል።


በዓሉ አንድነትን የሚያጠናክር፣ ጠንካራ የሥራ ባህልን የሚያበረታታ እና የተፈጥሮ ጥበቃን የሚያጠናክር በመሆኑ ከካፋ ብሔረሰብ በዓልነቱ ባለፈ የሀገርና የአለም ቅርስና ሀብት እንዲሆን ሰፊ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አቶ ፀጋዬ አሳስበዋል።
የካፋቾ ዘመን መለወጫ በዓል (የመኔ ሸድዬ ባሮ) መሠረቱን ሳይለቅ ለትውልድ እንዲተላለፍ በዞን ደረጃ እየተሠራ መሆኑን የገለፁት የካፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ተሾመ አምቦ ዘንድሮም ለዘጠነኛ ጊዜ በአደባባይ ለማክበር ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በዓሉ በሁሉም የካፋ ህዝብ በጋራ ያለምንም ልዩነት የሚከበር ታሪካዊ በዓል ሲሆን አለም አቀፋዊ እውቅና አግኝቶ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ለማስቻል ከተለያዩ ምሁራንና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን የተለያዩ ጥናቶች እየተሠሩ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በበዓሉ ንጉሱ የተራቡትን የሚመግቡበት (ጮንጎ) የተሰኘ ስርዓት የሚፈፀምበትና የተጣሉ የሚታረቁበት ስርዓት እንደሚፈፀም የገለፁት አቶ ተሾመ አሁንም በዓሉ በየዓመቱ ሲከበር ይህ ሥርዓት ይከወናል ብለዋል። ቀጣይ ይህን በዓል በሰፊው አስተዋውቆ ወደ ቱሪዝም በማሳደግ ህዝቡ ከዘርፉ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ  እንዲሆን የሚያስችሉ ሥራዎች እንደተጀመሩም ሃላፊው ገልፀዋል።

የዘንድሮው የ2016 ዓ.ም የካፊቾ ዘመን መለወጫ በዓል በቦንጋ ከተማ ከመስከረም 12 እስከ መስከረም 13/2016 ዓ.ም በፓናል ውይይትና በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበርም ጠቁመዋል።

    

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም