ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንደግፋለን - በጋምቤላ ክልል አስተያየት ሰጪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንደግፋለን - በጋምቤላ ክልል አስተያየት ሰጪዎች
ጋምቤላ ፤ መስከረም 9 / 2016(ኢዜአ)፡- በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ በጋምቤላ ክልል አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከጋምቤላ ክልል አራት ወረዳዎች በአጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ 144 ተወካዮችን በጋምቤላ ከተማ አስመርጧል።
የተመረጡት ተወካዮች ፤ ኮሚሽኑ በየደረጃው ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማመቻቸት ለጀመራቸው ስራዎች መሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ከተወካዮቹ ውስጥ አቶ ኡሞድ ኡቶው በሰጡት አስተያየት ፤ በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የተጀመረው የሰላም ግንባታ ሂደት በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነትና አብሮነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ መመቻቸቱ አሁን ላይ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር እየታዩ ያሉ ችግሮችን ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በአጀንዳ ልየታ ላይ እንዲሳተፉ በተሰጣቸው ኃላፊት መሰረት በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመደገፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ሁሉም ዜጋ በሰላም ወጥቶ ለመግባትና ሰርቶ ለመለወጥ የሰላም ግንባታን ቀዳሚ ተግባር አድርገን ልንሰራ ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላው ለአጀንዳ ልየታ የተመረጡት ወይዘሮ ቢዮንኬ ቶቤል ናቸው።
አቶ ቦሬ አባሚልኬካ በበኩላቸው፤ ልማትና እድገት ማምጣት የሚቻለው ሰላም ሲኖር መሆኑን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል እንደ ሀገር ሽማግሌ ለሰላም ግንባታ ጥረት ሲያደረጉ እንደነበር አስታውሰው ፤ በቀጣይም ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት በኮሚሽኑ አመቻቺነት ለሚካሄደው የምክክር መድረክ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያድረጉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በበኩላቸው፤ የክልሉ ህዝብ ችግሮችን ለይቶ በማውጣት ለሰላም ግንባታ ሂደቱ መሳካት የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በጋምቤላ ከተማ ትናንት በተካሄደው በአጀንዳ ልየታ መርሃ ግብር ላይ ከኢታንግ ፣ ከጎደሬ ፣ከመንገሺ ወረዳዎችና ከጋምቤላ ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ 144 ተወካዩች የተመረጡ ሲሆን፤ ዛሬ ደግሞ በሌሎች ወረዳዎች ተመሳሳይ ምርጫ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።