ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል ሊጎለብት ይገባል- የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል ሊጎለብት ይገባል- የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን
ጋምቤላ ፤ መስከረም 9/2016(ኢዜአ)፡- ችግሮችን በውይይትና በምክክር የመፍታት ባህልን በማጎልበት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሁሉም በጋራ ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አመለከተ።
በጋምቤላ ክልል በአጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የመምረጡ ሂደት ዛሬም ቀጥሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዳሉት፤ በሀገሪቱ እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል።
ለዚህም አለመግባባቶችን በውይይትና በምክክር የመፍታት ባህልን በማጎልበት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በጋራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር እየታዩ ያሉ ችግሮችን ህዝቡ ነቅሶ በማውጣትና እራሱም የመፍትሄው አካል እንዲሆን ኮሚሽኑ የማመቻቸት ስራ እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በጋምቤላ ክልል ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ያለው በአጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጡ ተግባር የዚሁ አንዱ አካል እንደሆነ አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ ዛሬ በኑዌር ዞን ከሚገኙ አምስት ወረዳዎች በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ 180 ተወካዮችን በማስመረጥ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።