በአፍሪካ የድህረ-ምርት ብክነትን በመቀነስ የምግብ ዋስትና እና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ይገባል - ኮሚሽነር ጆሴፍ ሳኮ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የድህረ-ምርት ብክነትን በመቀነስ የምግብ ዋስትና እና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ይገባል - ኮሚሽነር ጆሴፍ ሳኮ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 9/2016 (ኢዜአ) ፦ በአፍሪካ የድህረ-ምርት ብክነትን በመቀነስ የዜጎችን የምግብ ዋስትና እና ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ እንደሚገባ በአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ኮሚሽነር ጆሴፍ ሳኮ ገለጹ።
4ኛው የመላ አፍሪካ የድህረ-ምርት ጉባኤና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት እየተካሄደ ነው።
ጉባኤው "ዘላቂ የድህረ-ምርት አስተዳደር በአፍሪካ: የግብርና ንግድ ማሳደግ፥ የምግብ ደኅንነትና የተመጣጠነ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
ኮሚሽነር ጆሴፍ ሳኮ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የምርት ብክነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ አነስተኛ የእርሻ ኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማነስና ሌሎች ጉዳዮች በአህጉሪቱ ህዝብ የምግብ ደህንነት ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ ነው።
ጉባኤውም የምርት ብክነትን ጨምሮ በግብርና ዘርፍ የሚያጋጥመውን ችግር በተቀናጀ መልኩ ምላሽ መስጠት የሚያስችል መፍትሔ ላይ ለመምከር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በድህረ ምርት ወቅት 800 ሚሊየን ዜጎችን መመገብ የሚያስችል ምርት እንደሚባክን ጠቁመው፤ በአፍሪካም ከሚመረተው ሰብል 30 ከመቶ በላይ ምርት ይባክናል ብለዋል።
ይህን ምርት ከብክነት መታደግ ቢቻል በአህጉሪቱ ውስጥ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የምግብ ደህንነት ማረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍም ሆነ በአፍሪካ እያጋጠመ ያለው የምርት ብክነት፤ የምግብ ደህንነትና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአህጉሪቱን የምግብ ደህንነት በማረጋገጥና የግብርና ምርት ብክነትን በመቀነስ የዜጎችን የምግብ ዋስትና እና ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት አህጉራዊ ቢሮ ረዳት ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አበበ ኃይሌ፤ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የድህረ-ምርት ጉዳይን ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የምርት ብክነትን ለመቀነስም ቅንጅታዊ ትብብርን በማሳደግ የዜጎችን የምግብ ደህንነት ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በዓለም አቀፉ የሃብት ኢንስቲትዩት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር እና ምክትል ፕሬዚደንት ዋንጂራ ማታይ፣ የአፍሪካውያን የእርስ በርስ የግብርና ምርት ንግድን ማሳደግ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
አውሮፓውያን 80 በመቶ፤ ኤስያ ደግሞ 60 በመቶ የእርስ በእርስ የግብርና ምርት ንግድ እንደሚያደርጉ ጠቁመው፤ 15 ከመቶ ያልዘለለውን የአፍሪካ የእርስ በእርስ የግብርና ምርቶች ግብይት ማሻሻል እንደሚስፈልግም አንስተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር እና የኢትዮጵያ ድህረ-ምርት ብክነት ማህበር የስራ አስፈፃሚ አባል ዶክተር አሻግሬ ዘውዱ፤ ጉባኤው የአህጉሪቱን የ30 ከመቶ የድህረ ሰብል ምርት ብክነት ለመቀነስ የሚስችሉ ሃሳቦች ላይ ምክክር ይደረጋል ብለዋል።
ጉባኤውም ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የሚስተዋለውን የድህረ ምርት ብክነት መቀነስ የሚያስችል ስትራቴጂ በመቅረጽ ተግባራዊ እንዲሆን በር የከፈተ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ ትራክተርን ጨምሮ ለመካናይዜሽን የእርሻ ስራ የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ማድረጉ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ዛሬን ጨምሮ እስከ አርብ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ በአፍሪካ የሚስተዋለውን የምግብ እጥረትና የምርት ብክነት ችግርን የሚፈቱ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።
በጉባኤው የዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ተወካዮች፣ የአፍሪካ አገራት የግብርና ዘርፍ የስራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።