የቀይ ባህር ተለዋዋጭ የደኅንነት ጉዳዮችና ቀጣናዊ ትብብር ላይ ትኩረት ያደረገ ጉባኤ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 9/2016 (ኢዜአ)፦ የቀይ ባህር ተለዋዋጭ የደኅንነት ጉዳዮችና ቀጣናዊ ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረገ ጉባኤ ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።  

ጉባኤው “የቀይ ባህር የደኅንነት ሁኔታ፤ ቀጣናዊ ምክክርና ትብብር መልክዓ-ፖለቲካዊ መጠላለፍ በበዛበት ዓለም” በሚል መሪ ኃሳብ ነው የሚካሄደው።

ጉባኤው የተዘጋጀው በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትና የኢፌዴሪ መከላከያ ዋር ኮሌጅ ትብብር ነው።

ጉባኤው የቀይ ባህር ተለዋዋጭ የደኅንነት ጉዳዮችና ቀጣናዊ ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ የሚካሄድ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ገልጿል። 

በቀጣናው አሁን ያሉ የጸጥታ ሥጋቶች በቀይ ባህር ደኅንነት ሊኖረው ስለሚችለው ተጽዕኖና መፍትሔዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ተብሏል።

የቀጣናው አገራት ተቀራርበው የሚሰሩበትና ጠንካራ፣ ሁሉን አቀፍና ከሁኔታዎች ተለዋዋጭነት ጋር አብሮ የሚሄድ ቀጣናዊ የጸጥታ ትብብር ማዕቀፎችን ለመፍጠር የሚያስችሉ የፖሊሲ አማራጮች ላይም ይመክራል። 

የኢፌዴሪ መከላከያ ዋር ኮሌጅ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ፤ ጉባኤው የአkaባቢው አገራት የጸጥታ ሥጋቶችን በጋራ ለመፍታት በትብብር መሥራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ሕገ-ወጥ የሰዎችና የመሣሪያ ዝውውር እንዲሁም ሌሎች የጸጥታ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ስጋቶችን በጋራ መግታት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ምክክር ይደረጋል።

የምርምርና የፖሊሲ ተቋማት ተወካዮች፣ የፖሊሲ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ምሁራን፣ የአገራት አምባሳደሮችና ሌሎችም በጉባኤው እንደሚታደሙ ይጠበቃል።

የተለያዩ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም