አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ የተበረከተለትን የክብር ዶክትሬት ተረከበ - ኢዜአ አማርኛ
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ የተበረከተለትን የክብር ዶክትሬት ተረከበ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2016(ኢዜአ)፦ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ የተበረከተለትን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተረከበ።
ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ ተበርክቶለት የነበረውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በወቅቱ በስራ ምክንያት በአካል ተገኝቶ መቀበል ባይችልም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ተቀብላለት እንደነበር ይታወሳል።
በትናንትናው ዕለትም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዱጉማ አዱኛ በተገኙበት የክብር ዶክተሬቱንና እውቅናውን በአካል በተገኘበት ተበርክቶለታል።
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሃገሩን ወክሎ በተሳተፈባቸው ዓለምአቀፍ የውድድር መድረኮች በርካታ ድሎችን ያስመዘገበ ሲሆን፣ የሀገሩን ስም እና ሰንደቅ ዓላማም ማስጠራት ችሏል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ፣የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ፣ የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ አደ ስንቄዎች፣ የአትሌቱ ቤተሰቦች፣ የሙያ አጋሮቹና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መታደማቸውን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።