ቀጥታ፡

ጣሊያን ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትፈልግ ገለጸች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 09/2015 (ኢዜአ)፦ ጣሊያን ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት ፍላጎት እንዳላት አስታወቀች።

78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በኒው ዮርክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን የዘላቂ የልማት ግቦች የመሪዎች የፖለቲካ ፎረም እየተከናወነ ነው።

የጣሊያን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ በፎረሙ ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ከኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህና ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብሺር ኦማር ጋር የጋራ ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ በጣሊያንና በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ ሰላም፣ ደህንነትና ሽብርተኝነትን የመዋጋት ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት አገራት ልዑካን በተጠቀሱት መስኮች ያለውን ግንኙነት ለማጎልበት ጥረቶችን የሚደግፍ የጋራ ማዕቀፍ ለመፍጠር መስማማታቸውን ገልጿል።

የጣሊያን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ ጣሊያን ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

ከተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የአገራት መሪዎች የሚሳተፋባቸው የተለያዩ ውይይቶች በመደረግ ላይ ናቸው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከተለያዩ አገራት ልዑካን፣ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ከአጋር አካላት ተወካዮች ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

78ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ እስከ መስከረም 15/2016 ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም