የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ እንደሆነ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ እንደሆነ ገለጸ
አዲስ አበባ ፤መስከረም 8/2016(ኢዜአ)፦የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን የሕብረቱ የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን አስታወቁ።
78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ “ሰላም፣ ብልጽግና፣ ለውጥና ዘላቂነት” በሚል መሪ ሀሳብ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ይገኛል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ የጋራ ፍላጎቶች በሆኑ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ኮሚሽነር ጁታ ኢትዮጵያ ሰላምን በማጽናት ሂደት ውስጥ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር ስትራቴጂካዊ ትብብር ያለው የአውሮፓ ሕብረት ከአገሪቷ ጋር ላለው ግንኙነት ልዩ ቦታ እንደሚሰጥ ገልጸው የኢትዮጵያ መንግስት ትብብሩን ለማጠናከር ያለውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ ጽኑ የሆነ ቁርጠኝነት እንዳላትና ከሰላም የሚገኘውን ትሩፋት ለሌሎችም ለማጋራት እንደምትሰራ ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ለመልሶ ማቋቋምና መልሶ ግንባታ ስራዎች የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።