የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል - የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር - ኢዜአ አማርኛ
የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል - የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 8/2016 (ኢዜአ)፦ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል ሲሉ የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ኤንዲ አሰፋ ገለፁ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን የሚገኘው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርና በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ውሳኔ አሳልፏል።
ይህንንም ተከትሎ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ኤንዲ አሰፋ ሁለቱ ቅርሶች በዩኔስኮ መመዝገብ ቅርሶቹ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን ቅርሶቹን ክትትልና ጥበቃ እንዲኖራቸው በማድረግ የነበራቸውን ገፅታ የተሻለ እንዲሆን ያስችላል ያሉት የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ቅርሶቹን ለዓለም በማስተዋወቅ የአገርን ገፅታ በመገንባታ የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ያስችላልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በርካታ ቅርሶችን በዩኔስኮ ያስመዘገበች አገር እንደሆነች በማንሳት አገሪቱ ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ እንድትሆን ሁሉም ዜጋ አገሪቱን በማስተዋወቅ መሥራት አለበት ብለዋል።
ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ኢትዮጵያ ያላትን ቅርሶቹን ይበልጥ በማስተዋወቅና ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የበኩሉን እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርን ከ6 ሺህ በላይ ትክል ድንጋዮችን የያዘ ሲሆን፤ ለጥናትና ምርምር አድራጊዎች፣ ለውጭና አገር ውስጥ ጎብኚዎች ቀልብን የሚስቡ ገጽታዎችን የተላበሰ ነው።
ከዚህ ባሻገርም መልክዓ ምድሩ ጥብቅ ደን የያዘ ሲሆን ጥምር ግብርናም የሚካሄድበት መሆኑ ሌላው ልዩ የሚያደርገው ገጽታው ነው።
በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተለያዩ ብርቅዬ የእጽዋትና የዱር እንሰሳት ዝርያዎች እንዲሁም ከኢትዮጵያ በከፍታ ሁለተኛው የሆነው የቱሉ ዲምቱ ተራራ መገኛ መሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።