ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ ለ180 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ትኩረት ተደርጓል-የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት

አዳማ፤መስከረም 8/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት በተያዘው በጀት ዓመት አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት ለ180 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ።

የተቋሙን ያለፈው በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም የገመገመና የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ በአዳማ ተካሒዷል።

በውይይቱ ላይም በበጀት ዓመቱ 4ሺህ 672 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት ለዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር የኢንተርፕራይዞች ልማት የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሙጂያ ሀቢብ ገልጸዋል።

ወይዘሮ ሙጂያ አያይዘውም በበጀት ዓመቱ ከ17 ሺህ 360 የሚበልጡ ነባር ኢንተርፕራይዞችን የማምረት አቅም ለማጠናከር መታቀዱንም አስረድተዋል።

ሥራ አስፈፃሚዋ እንዳሉት ኢንተርፕራይዞቹ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚሰማሩ ሲሆን፤ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ገቢ ምርትን ለመተካት ይሰራሉ ብለዋል።

ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ኢንተርፕራይዞችም 37 ሚሊዮን ዶላር ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ ግብ ተቀምጧል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ በበኩላቸው  እንዳሉት ባለፈው ዓመት አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀትና ነባሮቹን በማጠናከር ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል።

ኢንተርፕራይዞቹ በ'ኢትዮጵያ ታምርት' ንቅናቄ የድርሻቸውን እንዲወጡ የማምረት አቅማቸውን በማሳደግ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተደረገው ጥረትም አበረታች ውጤት ማሳየታቸውን አስታውሰዋል።

ዶክተር አለባቸው አክለውም ኢንተርፕራይዞች ከ428 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመቱ ገቢ ምርቶችን ተክተው በሀገር ውስጥ ማምረት መቻላቸውንም ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም