ሀገራት በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንዲሠሩ የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራት በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንዲሠሩ የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 8/2016 (ኢዜአ)፦ ሀገራት በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንዲሠሩ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ጥሪ አቀረቡ።
አቶ ሰለሞን ሶካ "የመንግስታት፣ የሲቪል ማህበራት እና የንግድ ማህበረሰቦች ትብብር ዓለም አቀፍ የመረጃ ደህንነትን ለማረጋገጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ከመስከረም 7-9 /2016 በሩሲያ እየተካሄደ በሚገኘው 17ኛው ዓለም አቀፍ ፎረም ላይ የቪዲዮ መልእክት አስተላልፈዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በመልዕክታቸው በተለይም የሳይበር ቴክኖሎጂው በየጊዜው መራቀቅ የሰውን የአኗኗር ዘይቤ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አስተሳሰቦችን ጭምር እየቀየራቸው እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
የቴክኖሎጂው እያደገ መምጣት ለኢኮኖሚው፣ ለፖለቲካው፣ ለባህሉና ለማህበራዊ መስተጋብሩ አወንታዊ ተጽእኖ እንዳለው ሁሉ አሉታዊ ጎንም እንደሚኖረው አቶ ሰለሞን መጥቀሳቸውን አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
አቶ ሰለሞን አያይዘውም አሁን ላይ ሁሉም ሐገራት ተግባራቸውን ለማከናወንና ከሌላው ዓለም ለመገናኘት የዲጂታል ቴክኖሎጂን መጠቀም ግድ እያላቸው ከመምጣቱም በላይ አንድ ሐገር ደሴት ሆኖ ተገልሎ መኖር እንደማይችል ሁሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂው ያመጣቸውን መልካም አጋጣሚዎች እና የሚያስከትለውን የደህንነት ስጋት በጋራ መምከር አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
ድንበር የለሽ እና ወስብስብ ተፈጥሮ ያለውን የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ሐገራት በተናጠል በሚያደርጉት ጥረት ማረጋገጥ እንደማይችሉና ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ይኸውም ትብብር፤ እውቀታችንን፣ ልምዳችንን እና ሪሶርሳችንን በማስተባበር ደህንነቱ የተጠበቀ የሳይበር ዓለምን መፍጠር ያስችላል ሲሉ አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡
ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች የምትገኘው ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት አጀንዳን ፈጽሞ ቸል እንደማትል የገለጹት አቶ ሰለሞን፤ ለዚህም በዋናነት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ከማቋቋም አንስቶ፣ ፖሊሲዎችን መቅረጽ፣ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ መደንገግን እንዲሁም የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ይሁንና የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች ለመፍታት በተናጠል ከምናደርገው ጥረት ይልቅ ከተለያዩ ሐገራት ጋር በትብብር የምንፈጥረው አቅም የተሻለ በመሆኑ መንግስታት በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡