ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘርፈ ብዙ የልማት ተጠቃሚነት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2016(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘርፈ ብዙ የልማት ተጠቃሚነት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሕዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ዙር ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ጳጉሜ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ማብሰራቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያውያን የውስጥ ፈተናና የውጭ ጫናን ተቋቁመው በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸው ተባብረው በመሥራታቸው የተገኘ ስኬት መሆኑንም በወቅቱ ገልጸዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልለ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ለኢዜአ እንደገለጹት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ዙር ሙሌት ለመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ ብስራት ነው ብለዋል።

ግድቡ ግንባታው ከተጀመረ አንስቶ እስከ አሁን በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ እዚህ መድረሱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የለውጡ አመራር ቆራጥ ውሳኔ በማሳለፍ በግድቡ ግንባታ ሂደት ይታዩ የነበሩ ችግሮችን ቀርፎ ወደማገባደድ መድረሱንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያውያን ብርቱ ጥረት እየተገነባ የሚገኘው ይህ ግድብ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሁለት ተርባይኖች አማካይነት ወደ ሃይል ማመንጨት መግባቱም የኅብረት ሥራችን ውጤት ነው ብለዋል።

አራተኛና የመጨረሻ ዙር ሙሌት ደግሞ ተጨማሪ የሃይል ማመንጨት አቅም የሚፈጥርና ከፍተኛ ውሃ የተያዘበት በመሆኑ ለአካባቢው ትልቅ ፀጋ፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን ደግሞ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መፍጠሩን አስረድተዋል።

ግድቡ ለኢትዮጵያውያን የብርሃን ምንጭ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሃይልን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝና ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ሚናው የላቀ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ከሃይል አቅርቦት ባሻገር ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ተናግረዋል።

በግድቡ ምክንያት የተፈጠረውን ሰው ሰራሽ ሀይቅና ከ70 በላይ ደሴቶች ተከትሎ በርካታ የመዝናኛ ሥፍራዎች እንደሚኖሩ ገልጸው፤ ይህም ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ያደርገዋል ነው ያሉት።

ሰው ሰራሽ ሃይቁ ለአሳ ልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ በተጨባጭ እየታየ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ፤ ይህም ለክልሉ ህዝብና ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል።

ሕዳሴ ግድብ ይዞት የመጣው ዘርፈ ብዙ የልማት ዕድል የአካባቢው ወጣቶችንና ኢንቨስተሮችን ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል።

ግድቡ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይዞት የመጣውን የልማት ዕድል በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል የክልሉን ማኅበረሰብ እድገትና የአገርን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል ተቋማት ጋር በመቀናጀት ዕቅድ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ለዚህም ወጣቶች በቀጣይ ወደ አካባቢው የሚመጡ ጎብኝዎችን በአግባቡ እንዲያስተናግዱና በቱሪዝም ዘርፉ በስፋት እንዲሰማሩ ከቋንቋ ጀምሮ ሥልጠና እየወሰዱ ነው ብለዋል።

በአሳ ኃብት ልማት የሚሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ተለይተው አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑም ነው ርዕሰ መስተዳድር የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም