ዓለም እያጋጠማት ለሚገኘው አሳሳቢ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይገባል-የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ

395

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 8/2016 (ኢዜአ) ፦ ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እያጋጠማት የሚገኘውን ተጽእኖ ለመዋጋት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አሳሰቡ።

ዓለም አቀፍ ተቋማት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችንና ለውጦችን በሚመጥን መልኩ ራሳቸውን በማሻሻል ለሚታዩ ችግሮች የመፍትሄ አካል መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በኒውዮርክ ተጀምሯል።

በጉባኤው ከ140 በላይ የሀገራት መሪዎች እየተሳተፉ ሲሆን አሳሳቢ በሆኑና ምላሽ በሚሹ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ይገኛሉ።

የመክፈቻ ንግግር በማድረግ ጉባኤውን ያስጀመሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

ዓለም በበርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች እየተፈተነች ትገኛለች ያሉት ዋና ጸሐፊው የአየር ንብረት ለውጡ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ የሰው ህይወት እየቀጠፈ እና ሰዎችን ከቀያቸው እያፈናቀለ ይገኛል ብለዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ምክንያት ዓለም ለችግር መጋለጧን ጠቅሰው ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖዎችን ለመዋጋት በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የአየር ንብረት ለውጡ በተለይ በታዳጊ ሀገራት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው ያሉት ዋና ጸሀፊው ለዚህም ያደጉ ሀገራት የሚለቁትን የካርበን መጠን ለመቀነስ ከዚህ ቀደም የተደረሰውን ስምምነት ማክበር ይገባቸዋል ሲሉም ገልጸዋል።

ሀገራት የሚለቁትን የካርበን መጠን ለመቀነስ ከነዳጅና የድንጋይ ከሰል ሀይል ፊታቸውን ወደ ታዳሽ ሀይል ማዞር እንዳለባቸው ጠቁመው የታዳሽ ሀይልን ማስፋፋት ዋነኛው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ መቀነሻ መንገድ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ያደጉ ሀገራት የራሳቸውን የካርበን ልቀት ከመቀነስ ባለፈ ለታዳጊ ሀገራት የአረንጓዴ ልማትና የታዳሽ ሀይል መስፋፋት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ የሰላምና የጸጥታ ሁኔታ በፍጥነት እየተቀየረ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ጸሀፊው የጸጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ማሻሻያ ሳያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል።

ለዚህም ዓለም አቀፍ ተቋማት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችንና ለውጦችን በሚመጥን መልኩ ራሳቸውን በማሻሻል ለሚታዩ ችግሮች የመፍትሄ አካል መሆን እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።

በመሆኑም እየተወሳሰበ የመጣውን ዓለም አቀፍ የሰላምና ጸጥታ ችግር ለመፍታት የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚገባቸውም ዋና ጸሐፊው ያሳሰቡት።

በተለይ የጸጥታው ምክር ቤት ዓለም አቀፍ የሰላምና የጸጥታ የፋይናንስ ስርዓቱን እንደገና መፈተሽ አለበት ሲሉም አሳስበዋል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዓለምን እየቀየራት እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን ይህን መቆጣጠር የሚችል ዓለም አቀፍ ተቋም ማቋቋም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በዚህ ዙሪያም ለሚደረግ ምክክር የተባበሩት መንግስታት ድረጅተ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም