የአባቱን የጀግንነት ፈለግ የተከተለው ዳግም ኤቢሳ

በኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት ታሪክ ለሀገር ክብር፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን ጠብቆ ለማቆየት የተዋደቁ፣ ጀግንነትን የተዋረሱ እና መስዋዕትነት የከፈሉ ቤተሰቦች ማግኘት የተለመደ ነው።

በየዘመኑ ለአገር ሉዓላዊነት፣ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ዘብ የቆሙ ወታደሮች ጀግንነታችውን ለልጆቻቸው አውርሰዋል፤ ልጆችም የአባትና አያቶቻቸውን ፈለግ በመከተል የራሳቸውን የጀግንነት አሻራ ያሳርፋሉ።

ለእናት አገር ዘብ መቆምን በትውልድ ቅብብሎሽ ካስቀጠሉ ቤተሰቦች መካከል የወይዘሮ እሙዬ ፈለቀ ባለቤት ኮሎኔል ኤቢሳ ታይሳ እና ልጃቸው ዳግም ኤቢሳ ይገኙበታል።

"እኛ የመከላከያ ሰራዊት ቤተሰብ ነን" የሚሉት ወይዘሮ እሙዬ ፈለቀ፣ ባለቤታቸው ኮሎኔል ኤቢሳ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አገልግሎ ለሀገሩ ክብር በጀግንነት መሰዋቱን ያነሳሉ።


 

የጀግና አባቱን ገድል እየሰማ ያደገውና የሀገር ፍቅርን የወረሰው ልጃቸው ዳግም ኤቢሳ ደግሞ በጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በመሰረታዊ ወታደርነት ተመርቋል።

ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ጦላይ በመሄድ በልጃቸው ምርቃት ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ እሙዬ ፈለቀ፣ "ልጄ የአባቱን የኮሎኔል ኤቢሳ ታይሳ ጀግንነትና የሀገር ፍቅር ለመከተል ከፍተኛ ስሜት ነበረው" ይላሉ።

"የጀግና ልጅ ጀግና ነውና ልጄም ሰራዊትን በመቀላቀል ጀግንነቱን በተግባር አረጋግጧል" ሲሉም ይናገራሉ።

ባለቤታቸው እና ልጃቸው ለሀገር ክብር ዘብ በመሆናቸውም የላቀ ክብርና ኩራት እንደሚሰማቸው የሚያነሱት ወይዘሮ እሙዬ፤ ልጃቸውን "እንደ አባትህ ጀግና ሁን" እያሉ ጀግንነትን እንዲላበስ ማድረጋቸውንም ይገልጻሉ።

"ልጄ የአባቱን ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሶ በማየቴ ከፍተኛ ኩራት ተሰምቶኛል" ያሉት እናት፣ ሀገርን በቅንነትና ታማኝነት በማገልገል የአባቱን የጀግንነት ታሪክ እንዲያስቀጥል መምከራቸውንም አንስተዋል።

ባለቤታቸው ለከፈለው መስዋዕትነትም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለቤተሰቡ ተገቢውን ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

መሰረታዊ ወታደር ዳግም ኤቢሳ በበኩሉ በማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ወታደራዊ ትምህርትና ስልጠና ወስዶ ከጓዶቹ ጋር በመመረቁ ተደስቷል።

"የእናት ሀገሬን ሉዓላዊነት አንድነት በመጠበቅ የአባቴን አሻራ ለማስቀጠል ዝግጁ ነኝ" ብሏል።

ወታደራዊ ግዳጅን በብቃት መወጣት የሚያስችል ትምህርትና ስልጠና መውሰዱን የሚናገረው ዳግም ኤቢሳ፣ እንደ አባቱ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ሀገሩን ለማገልገል ያለውን ወኔና ቁርጠኝነትም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም