ቀጥታ፡

ችግሮችን በውይይት በመፍታት እንደሀገር ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ሁሉም በትብብር ሊሰራ ይገባል-ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን

ጋምቤላ ፤ መስከረም 8/2016 (ኢዜአ) ፦ ችግሮችን በውይይት በመፍታት እንደሀገር ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ሁሉም ዜጋ በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በጋምቤላ ክልል በአጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮችን የመምረጥ መርሃ ግብር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ሰላም አይነተኛ መሳሪያ ነው።

አለመግባባቶችን በውይይት እና በምክክር በመፍታት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ ወደ ልማት በመቀየር አገርንና ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው በሁሉም አካባቢዎች የተረጋጋና ዘላቂ ሰላም ማስፈን ሲቻል መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን ገልጸዋል።

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ስለሆነም ኮሚሽኑ ለጀመራቸው ሥራዎች መቃናት መላው የጋምቤላ ብሎም የሀገሪቱ ህዝቦች በቅንነት ተባብረው መስራት እንዳለባቸው ነው ዋና ኮሚሽነሩ ያስገነዘቡት።

በጋምቤላ ክልል በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ አካላትን ለመምረጥ ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት እየተካሄደ ባለው መርሀ ግብርም የህብረተሰብ ተወካዮች በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዛሬው ዕለት ከጋምቤላ ከተማ አስተዳደር፣ ከጎደሬ፣ መንገሺ እና ኢታንግ ልዩ ወረዳዎች ከተለያዩ የማህበረሰብ አደረጃጀቶች የተውጣጡ ተወካዮች በቀጣይ በሚካሄድ አጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮችን እንደሚመርጡ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም