በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተመዘገበው ውጤት በትብብር ከተሰራ በሁሉም መስኮች ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ ነው- ከንቲባዎች

310

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 7/2016 (ኢዜአ)፦ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ- ግብር የተመዘገበው ውጤት በትብብር ከተሰራ በሁሉም መስኮች ስኬታማ በመሆን የኢትዮጵያን ብልጽግና ማሳካት እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች ከንቲባዎች ተናገሩ።

የሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ ማጠቃለያ መርሃ -ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተካሂዷል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ጆጎ ተፋሰስ በተካሄደው የማጠቃለያ መርሃ- ግብር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የሁሉም ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ከንቲባዎችና የግብርና ቢሮ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በአዲስ አበባ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ከ17 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ከዕቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እንደ ሀገር የተከናወነው ስራና የተመዘገበው ውጤት በትብብር ከተሰራ በሁሉም መስክ ስኬታማ በመሆን የኢትዮጵያን ብልጽግና ማሳካት እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር፤ በድሬዳዋ በዘንደሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ - ግብር ከዕቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።


 

ከጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ልዑካን ጋር ጭምር ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰው የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራም እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ መተከል በጀመረው አረንጓዴ አሻራ ከተሞች በርሃማነትን መከላከል እና አየር ንብረት ልውጥን  ከመቋቋም አኳያ የራሱ ሚና እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል። 

ሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር "ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፋር ክልል በመገኘት ማስጀመራቸው ይታወሳል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ዘንድሮን ጨምሮ በአራት ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።

በእቅዱ መሰረት የሚተከሉት ችግኞች 60 በመቶ ለጥምር ደን እርሻ፣ 35 በመቶ ለደን እና 5 በመቶ ለከተማ ውበት የሚውሉ ይሆናሉ።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም