የካፋቾ ዘመን መለወጫ (የመኔ ሸድዬ ባሮ) በዓል ታሪካዊ ዳራውን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሰራ ነው- መምሪያው - ኢዜአ አማርኛ
የካፋቾ ዘመን መለወጫ (የመኔ ሸድዬ ባሮ) በዓል ታሪካዊ ዳራውን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሰራ ነው- መምሪያው
ቦንጋ መስከረም 7 ቀን 2016 (ኢዜአ) ....የካፋቾ ዘመን መለወጫ በዓል ታሪካዊ ዳራውን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የካፋ ዞን ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።
በዓሉ መስከረም 13 ቀን 2016 ዓም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጲያ ህዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ ደምቀት እንደሚከበርም ተጠቁሟል።
አሮጌው አመት ተገባዶ መስከረም ሲመጣ በተለይ በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል በሚገኙ አብዛኞቹ ብሔረሰቦች ባህላዊ የዘመን መለወጫ በዓልን እንደየማህበረሰቡ ትውፊት በድምቀት ያከብራሉ።
ከነዚህም መካከል አንዱ የሆነው የካፋ ብሔረሰብ ከሚታወቅባቸው ቱባ ባህልና እሴቶች መካከል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ባህላዊ የዘመን መለወጫ (የመኔ ሸድዬ ባሮ) በዓል ነው።
ይህ በዓል ከአዝመራ ወቅት መገባደድ ጋር ተያይዞ በመስከረም ወር የሚከበር ታላቅ በዓል መሆኑን የመምሪያው ሀላፊ አቶ ተሾመ አምቦ ገልፀዋል።
በዓሉ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ሲሆን ሳይበረዝ ታሪካዊ ዳራውን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በየደረጃው ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን መሸጋገሪያ በመሆኑ የተጣላ የሚታረቅበት እንዲሁም የእርስበእርስ ትስስሩን የሚያጠናክርበት ታላቅ በዓል መሆኑንም አቶ ተሾመ ተናግረዋል።
በዓሉን ለማክበር የብሔረሰቡ ተወላጆች ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር የሚሰበሰቡ ሲሆን በዓሉም አዝመራን መነሻ ባደረገ የዘመን ቀመር የሚከናወን መሆኑንም አንስተዋል።
ዘንድሮም በዓሉን ከበፊቱ በተለየ መልኩ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ሰፊ ዝግጅት መደረጉንም የመምሪያው ሀላፊ ጠቁመዋል።
በዓሉ ጥንት በካፋ ንጉስ ዘመን በድምቀት ይከበረ የነበረ ሲሆን በመሀል ከመቶ ዓመት በላይ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይከበር መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የካፋ፣ጫራ እና ናኦ የባህል ምክርቤት አባል አቶ ፀጋዬ ወልደማሪያም ናቸው።
በዓሉ ዳግም መከበር በጀመረባቸው ካለፉት ስምንት ዓመታት ወዲህ ሰፊ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
የካፋ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል እርቅ የሚወርድበት እና ሰላም የሚሰፍንበት ትልቅ በዓል በመሆኑ ይህን እሴት ለወጣቱ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ባህሉን በጥናት በማስደገፍ ተሰንዶ እንዲቀመጥና ቀጣዩ ትውልድ ተገንዝቦት እንዲያዘልቀው የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዞኑ የዴቻ ወረደ አስተዳዳሪ አቶ ወንዱ ታደለ በበኩላቸው የዘንድሮውን የካፍቾ የዘመን መለወጫ በዓልን ሳይበረዝ ለትውልድ ለማሽጋገር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዓሉ በወረዳና ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች መስከረም 10 ላይ የሚከበር ሲሆን ማጠቃልያውና ዋናው በዓል ደግሞ በቦንጋ ከተማ "ቦንጌ ሻንቤቶ" መስከረም 13 ቀን 2016 ቀን ላይ ይከበራል።