በህዝቦቿ የተባበረ ብርቱ ጥረት ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ እናስረክባለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
በህዝቦቿ የተባበረ ብርቱ ጥረት ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ እናስረክባለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 7/2016 (ኢዜአ) ፦ በህዝቦቿ የተባበረ ብርቱ ጥረት ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ እናስረክባለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
የሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ማጠቃለያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተካሂዷል።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሎሜ ወረዳ ጆጎ ተፋሰስ በተካሄደው የማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የሁሉም ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ስላለው ተፅዕኖ በርካታ ዓለም አቀፍ ውይይቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ሆኖም ተፅዕኖውን ለመቋቋም ወደ ተግባር በመግባት በኩል ብዙ መጓዝ አለመቻሉን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በማስጀመር ተፅዕኖውን ለመቋቋም ተምሳሌታዊ የተግባር እርምጃ ውስጥ መግባቷን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ እስካሁን በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውንም ጠቅሰዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን በማንሳት፤ በሁለቱም ምዕራፎች የተተከሉ ችግኞች ብዛት 50 ቢሊዮን ለማድረስ እቅድ መያዙን ነው የገለጹት።
ከአራት ዓመታት በፊት የጆጎ ተፋሰስ አካባቢ ምድረ በዳ እና ገላጣ ስፍራ እንደነበር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፤ አሁን ላይ አካባቢው በአረንጓዴ ተሸፍኗል ብለዋል።
ለዚህ ስኬት የአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ጠቅሰው የአረንጓዴ ልማቱን መሰረት በማድረግም ማህበረሰቡ የንብ ማነብ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በአረንጓዴ ልማት የአፈር መሸርሸርን ማስቀረት፣ የዝናብ መጠንን መጨመርና ስርዓተ ምህዳርን ማስተካከል መቻሉን ገልጸው፤ ከዚህም ባለፈ ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት።
በቀጣይም የፍራፍሬ፣ የቡና፣ የሻይ እና ሌሎች ገበያ ተኮር የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላሳየው ብርቱ ጥረትና ላስመዘገበው ስኬት መንግስት ከፍተኛ ክብር እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
በቀጣይም በአረንጓዴ አሻራ፣ በህዳሴ ግድብ፣ በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን በሁሉም ዘርፍ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ስኬት አይቀሬነት የሚያረጋግጡ ውጤታማ ተግባራት በመንግስትና በህዝብ ትብብር እየተከናወኑ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞ የማፅናትና ብልፅግናዋን የማረጋገጥ ጉዞን የሚያስቆም አንዳችም ምድራዊ ሃይል አይኖርም ሲሉም በአፅንኦት ተናግረዋል።
በህዝቦቿ የተባበረ ብርቱ ጥረት ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ እናስረክባለን ሲሉም ተናግረዋል።
ሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር "ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፋር ክልል በመገኘት ማስጀመራቸው ይታወሳል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዘንድሮን ጨምሮ በአራት ተከታታይ ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።
በእቅዱ መሰረት የሚተከሉት ችግኞች 60 በመቶ ለጥምር ደን እርሻ፣ 35 በመቶ ለደን እና 5 በመቶ ለከተማ ውበት የሚውሉ ይሆናሉ።