በኢትዮጵያ ተላላፊ በሽታዎች ሳይከሰቱ ቀድሞ መከላከል የሚያስችል ፕሮጀክት ተግባራዊ መደረግ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ተላላፊ በሽታዎች ሳይከሰቱ ቀድሞ መከላከል የሚያስችል ፕሮጀክት ተግባራዊ መደረግ ጀመረ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 7/2016 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ ተላላፊ በሽታዎች ሳይከሰቱ ቀድሞ መለየትና መከላከል የሚያስችል /ኢፒጄን ኢትዮጵያ/ የተሰኘ ፕሮጀክት ተግባራዊ መደረግ ጀመረ።
ፕሮጀክቱ በ4 ሚሊዮን ዩሮ ለአምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ፣ ማንኛውንም በሽታ በዘረመል ደረጃ ማወቅ የሚያስችልና በመላ አገሪቱ የሚተገበር መሆኑም ተጠቁሟል።
የፕሮጀክቱን ትግበራ አስመልክቶ ባለድርሻ አካላት ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት አድርገዋል።
ፕሮጀክቱን በኢትዮጵያ የሚገኙ ተመራማሪዎች አውሮፓ ከሚገኙ ተቋማት ጋር በመሆን ከአውሮፓ ህብረት የ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ተወዳድረው ያስገኙት ሲሆን 4 ሚሊዮን ዩሮው ለኢትዮጵያ፤ ቀሪው ለሌሎች አገራት ተሰጥቷል።
በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና በአውሮፓ የሚገኙ ተመራማሪዎች በጋራ በመሆን ድጋፉን ተወዳድረው ማስገኘታቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረገው ይህ ፕሮጀክት በሽታን ቀድሞ መለየት የሚያስችል እና አገራዊ የምርምርና ጥናት አቅምን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
በፕሮጀክቱም የዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟሉ ላቦራቶሪዎች ማጠናከርና ከ15 በላይ የ3ኛ ዲግሪ የጤና ባለሙያዎች በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ከፍተኛ ተቋማት ማሰልጠን ያስችላል ብለዋል።
ከዚህ በፊት የተለያዩ አዳዲስ በሽታዎች ሲከሰቱ ውጪ አገራት ተልከው የላቦራቶሪ ምርምራ ይካሄድ እንደ ነበር ጠቁመው አሁን በአገር ውስጥ የመስራት አቅም ለመፍጠር ያግዛልም ነው ያሉት።
ፕሮጀክቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ300 በላይ ሆስፒታሎች እና ጤና ተቋማት መረጃ እንደሚሰበስብ እና ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
ጥናቱን ካካሄዱ ተመራማሪዎች መካከል በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ዳዊት ወልዳይ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ተላላፊ በሽታዎችን ሳይከሰቱ ቀድሞ መከላከል የሚያስችል ነው።
በኢትዮጵያ የሚገኙ ተመራማሪዎች አውሮፓ ውስጥ ከሚገኝ የምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ተወዳድረው ማሸናፋቸውን ተከትሎ ፕሮጀክቱን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ አስችሏል።
የጤና ሚኒስትር አማካሪ ዶክተር መብራቱ ማሴቦ ፕሮጀክቱ መንግስት በሽታን ለመከላከል በአገሪቱ ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘውን ፖሊሲ የሚደግፍ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት አገራዊ አቅምን ለማሳደግ በአገር ውስጥ በሽታን መለየት የሚያስችሉ የተለያዩ ላቦራቶሪዎች፣ ተቋማት እና የሰው ሃይል እንዲሁም የበሽታዎች ቅኝት አቅም ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ ከኢትዮጵያ አልፎ ሌሎች አፍሪካ አገራትንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።