ባለፈው ነሐሴ ወር ለውጭ ገበያ ከቀረበ 27 ሺህ ቶን ቡና 140 ሚልዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 7/2016 (ኢዜአ) ፦ባለፈው ነሐሴ ወር ለውጭ ገበያ ከቀረበ 27 ሺህ ቶን ቡና 140 ሚልዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ፤ የቡና ምርት በዓመት በአማካይ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል። 

በ2015 በጀት ዓመት ሳዑዲ አረቢያ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ኮሪያ፣ ቤልጅየም፣ ጃፓን እና ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ የኢትዮጵያን ቡና በብዛት ከገዙ አገራት መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በዚህም አጠቃላይ ከ240 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ መቅረቡን ዶክተር አዱኛ ገልጸዋል።

የውጭ ምንዛሪ ግኝቱም በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም 1 ነጥብ 34 ቢልዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት እስካሁን የኢትዮጵያ ቡና አቅርቦት 18 በመቶ መጨመሩን ጠቅሰው ውጤቱ የተገኘው የሚቀያየረውን ገበያ የሚቋቋም ጥራት ያለው ምርት ማቅረብ በመቻሉ ነው ብለዋል።


 

በዚህም በባለፈው ነሐሴ ወር ብቻ 27 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ 140 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

በ2016 በጀት አመት 350 ሺህ ቶን ቡና በመላክ 1 ነጥብ 75 ቢልዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል።

የተያዘውን እቅድ ለማሳካትም ከአርሶ አደሮች ጀምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2014 በጀት ዓመት ከቡና የወጪ ንግድ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ  በማግኘት ትልቅ ስኬት መመዝገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ከቡና የሚገኘውን ገቢ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም